
ባሕር ዳር: ጥር 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ ክብረ በዓላት በሚያደምቋት ኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ወርኃ ጥር የተለየ ድባብ አለው፡፡ በወርኃ ጥር በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች የተለያዩ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት በድምቀት ይከበሩበታል፡፡
ለቱሪዝም ዘርፉ የጎላ አበርክቶ ያላቸው እነዚህ ክብረ በዓላት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ተቀዛቅዘው ቆይተዋል፡፡ ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ የጎዳውን እና ተደጋጋሚ ግጭት እና ጦርነት የበዛበትን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ መልሶ እንዲያንሰራራ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓቱን መጠቀም እንደሚገባ ይታመናል፡፡
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ወርኃ ጥርን ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መልሶ ማንሰራራት መጠቀም እንደሚገባ አስታውቋል፡፡ የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አበበ እምቢያለ በወርኃ ጥር የሚከበሩ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት የቱሪም እንቅስቃሴውን እንዲያነቃቁ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ጥርን በባሕር ዳር፣ ጥምቀትን በጎንደር፣ ጥምቀት በኢራምቡቲ፣ የጊዮን በዓል በሰከላ፣ አስተርዮን በመርጦ ለማሪያም፣ የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ዓመታዊ ክብረ በዓል በእንጅባራ፣ መርቆሪዮስ በደብረ ታቦር እና መካነ ኢየሱስ እና ሌሎች በርካታ ክብረ በዓላት በወርሃ ጥር ይከወናሉ፡፡ እነዚህን ክብረ በዓላት የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንዲያነቃቁ እና የክልሉን ገጽታ በበጎ ጎኑ እንዲያስተዋውቁ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው፡፡
“ጥርን ለቱሪዝም አቅዶ እና አልሞ መጠቀም ያስፈልጋል” ያሉት አቶ አበበ በቅርቡ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በላሊበላ የተከበረው የልደት በዓል ስኬት አስተማሪ ነበር ብለዋል፡፡ ጥምቀትን በጎንደር እና ጥርን በባሕር ዳር በተለየ መልኩ ለማክበር ከተሞቹ የሚያደርጉትን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ቢሯቸው እና የክልሉ መንግሥት በሙሉ አቅሙ እያገዘ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ አበበ ገለጻ በወርኃ ጥር የሚከበሩት እነዚህ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት ከተጠናቁ በኋላም የድንቅ ምድር አማራ እና የክልሉ ወይዘሪት ቱሪዝም አማራ ቁጥር ሁለት መርሐ ግብሮች ይካሄዳሉ ብለዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በጎንደር ከተማ የተካሄደው የድንቅ ምድር አማራ እና የወይዘሪት ቱሪዝም አማራ ቁጥር አንድ ዝግጅቶች የክልሉን የቱሪዝም ገጽታ በበጎ ጎኑ ያስተዋወቀ ነበር ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!