
ባሕር ዳር፡ ጥር 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው የባሕር በር ስምምነት በቅንነት የሚወሰድ ሀገራዊ አጀንዳ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ተናገሩ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአባላቱ ጋር ምክክር አድርጓል።
በኢትዮጵያና ሶማሊላንድ መካከል በተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት ዙሪያም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከውይይቱ በኋላ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በመግባቢያ ስምምነቱ ዙሪያ የተሰጠው ማብራሪያ የሚሰሙ ብዥታዎችን የሚያጠራ ብሎም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመቆም የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ፤ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተሰጠው ዝርዝር ማብራሪያ ብዥታዎችን የሚያጠራ እና በጋራ ጉዳዮች የጋራ አቋም ለመያዝ የሚያስችል ነው ብለዋል። ለኢትዮጵያ የባሕር በር አስፈላጊነትና ለቀጣናዊ የልማት ትስስር ስምምነቱ የሚኖረውን ሚና በግልጽ የተረዳንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና እድገት የሚሻ በመሆኑ፤ በመንግሥት የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል። በመሆኑም የተደረሰው ስምምነት የሀገሪቷን ብሔራዊ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን በጥንቃቄ መመራት አለበት ነው ያሉት።
የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ መለሰ ዓለሙ፤ የባህር በር ስምምነት ማዕቀፍ ዝርዝር መረጃ ቀርቦ ውይይት መደረጉንና ፓርቲዎችም ስምምነቱን አስመልክቶ ያላቸውን በጎ እና አዎንታዊ ምላሸ መስጠታቸውን አንስተዋል።
ፖለቲካ ፓርቲዎች የግል ፖለቲካዊ አቋም ቢኖራቸውም በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ግን ልዩነት የላቸውም ሲሉ አረጋግጠዋል። የኢዜማ ምክትል መሪ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን፤ የውይይት መድረኩ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ያገኘንበት ነው ብለዋል።
ፓርቲያቸው በተለያዩ ሀገራዊ የፖሊሲ ጉዳዮች ከመንግሥትና ሌሎች ፓርቲዎች ጋር ልዩነት ቢኖረውም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እና አጀንዳዎች ላይ ግን የተለየ አቋም እንደሌለው ተናግረዋል።
የባህር በር ጉዳይም የኢትዮጵያውያን የዘመናት ምኞት በመሆኑ ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን የሁላችንም መልካም ምኞት ነው ብለዋል። በቀድሞ ጊዜ የአሰብ አስተዳዳሪ እንደነበሩ የሚናገሩት የአፋር ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር መሃሙዳ ጋዓስ፤ ኢትዮጵያ የነበራትን የባህር በር በማጣቷ ብዙ ችግር ማስተናገዷን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ባለቤት የሚያደርጋት ጥረት መጀመሩ የሚደነቅ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከኢትዮጵያ አሁናዊ ኢኮኖሚ ዕድገት አኳያ አማራጭ ወደቦችን ማስፋት ተገቢ በመሆኑ ከሶማሊላንድ ጋር የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን የጋራ ፍላጎታችን ነው ብለዋል።
የአንዲት ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ሲሳይ ደጉ፤ ከሶማሊላንድ ጋር የተደረሰው ስምምነት ይበል የሚያሰኝ እና ለቀጣናው ትብብርም መልካም ጅማሮ መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም የባሕር በር ስምምነቱን ተግባራዊነት እንደሚደግፉ ገልጸው፤ መንግሥት ውስጣዊ አንድነትን የሚሸረሽሩ የሰላምና ጸጥታ ሥራዎችን መፍታት እንዳለበት ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!