የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት እንዲለማ የተመረጠውን የሎጎ ሐይቅ ጎበኙ።

22

ባሕር ዳር: ጥር 01/2016 ዓ.ም (አማኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሀሳብ አመንጭነት በሦስተኛው ዙር የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት እንዲለማ የተመረጠውን የሎጎ ሐይቅ ጎብኝተዋል።

ሎጎ ሐይቅ በደቡብ ወሎ ዞን ከሚገኙ አራት የተፈጥሮ ሐይቆች አንዱ ነው። ከደሴ ከተማ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን አርዲቦ፣ ማይባር እና ጎልቦ ከተባሉት በዞኑ የሚገኙ ሐይቆች መካከል በስፋቱና በጥልቀቱ ቀዳሚ ደረጃን ይይዛል። 23 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ስፋትና ከ70 እስከ 88 ሜትር የሚደርስ ጥልቀትም አለው።

በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ለማልማት የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተደረጉለት ነው። በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን፣ በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኀበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እና ሌሎችም የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች አካባቢውን ተንቀሳቅሰው ጎብኝተዋል።

በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ሊከናወን የታቀደው ግንባታ በአካባቢው የሚገኙ የቱሪዝም መስህብ ሀብቶችን ለማስተዋወቅ እና በቀጣናው ያለውን የቱሪስት ፍስሰት የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መኾኑን አመራሮቹ ገልጸዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብም ለግንባታው በመተባበር የጸጋው ተጠቃሚ መኾን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የክልሉ መንግሥት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ግንባታው ፍጻሜ ድረስ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ከፍተኛ አመራሮች ማረጋገጣቸውን የደቡብ ወሎ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ አመላክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለአፍሪካ ዋንጫ የተለያዩ ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖች አቢጃን እየገቡ ነው።
Next articleየኢትዮ-ሶማሊላንድ የባሕር በር ስምምነት በቅንነት የሚወሰድና የሚደገፍ ሀገራዊ አጀንዳ ነው።