
ባሕር ዳር: ጥር 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኮትዲቯር አስተናጋጅነት ለሚደረገው የ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የተለያዩ ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖች ወደ አቢጃን እየገቡ ይገኛሉ፡፡
ትናንት ምሽት የካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን ኮትዲቯር ገብቷል። የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ከልዑካን ቡድኑ ጋር አቢጃን ገብተዋል፡፡
የካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚ የግብፅ ብሔራዊ ቡድንም ከደቂቃዎች በፊት ኮትዲቯር ደርሷል፡፡ የሊቨርፑሉን ኮከብ ሞሀመድ ሳላህ ያካተቱት ፈርዖኖቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በመጪው እሁድ ከሞዛምቢክ ጋር ያደርጋሉ፡፡
በተመሳሳይ የደቡብ አፍሪካ እና ታንዛኒያ ብሔራዊ ቡድንም በትናንትናው እለት ወደ አዘጋጇ ሀገር ገብተዋል። የጊኒ ቢሳው ብሔራዊ ቡድን ቀደም ሲል ወደ ኮትዲቯር ያቀና የመጀመሪያው ብሔራዊ ቡድን መኾኑ የሚታወስ ነው፡፡
የ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ቅዳሜ አዘጋጇ ኮትዲቯር ከጊኒ ቢሳው ጋር ቀን 11፡00 ሰዓት ላይ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀምራል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!