
ባሕር ዳር: ጥር 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዲፕሎማሲ ሳምንት የአዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ለማስፋትና ለማፅናት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መኾኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዶክተር መለስ ዓለም፤ በነገው እለት በይፋ የሚከፈተውን የዲፕሎማሲ ሳምንት በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የሕዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ መኾኑን ጠቅሰው ከአፍሪካ መዲና እስከ ዓለም የሚደርሰው የዲፕሎማሲ ሳምንት ነገ በይፋ ይከፈታል ብለዋል።
አዲስ አበባ በዓለም ላይ ካሉ ሦስት የዲፕሎማሲ ማዕከላት አንዷ መሆኗን የገለጹት አምባሳደር ዶክተር መለስ፣ ይሄንን ለማስቀጠል ተጨማሪ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል። በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ በባለብዙ ወገንና ሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ተጨባጭ ውጤት የተመዘገበበት መኾኑንም ገልጸዋል።
በዲፕሎማሲ ሳምንት ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ ኤምባሲዎች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች በዓውደ ርዕይው ላይ ይሳተፋሉ ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከፍ የሚያደርጉ የዲፕሎማሲ ሥራዎች በማከናወናቸው በርካታ ስኬቶች እየተመዘገቡ መኾኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል የሆነችበት መንገድም የእርሳቸው ጥረት ታክሎበት የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ሥራ ውጤታማነት ማሳያ ነው ብለዋል። በመሆኑም በነገው እለት በይፋ የሚከፈተው የዲፕሎማሲ ሳምንት የአዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማእከልነት ለማስፋትና ለማፅናት የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።
በመሆኑም አውደ ርእዩን በመጎብኘት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሀገሩ አምባሳደር ለመኾን ቃል መግባት ይኖርበታል ነው ያሉት። በዲፕሎማሲ ሳምንቱ ስድስት ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርባሉ፤ የፓናል ውይይቶችና የሁለት መጻሕፍት የምርቃት ፕሮግራም እንደሚኖርም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል። አውደ ርእዩን የታሪክ ምሁራንና ተመራማሪዎች እንዲጎበኙም አምባሳደሩ ጥሪ ቀርቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!