ድርቁን ለመቋቋም የበጋ መስኖ ልማትን ቀዳሚ ምርጫ በማድረግ እየሠራ መኾኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ፡፡

12

ሰቆጣ: ጥር 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የበጋ መስኖ ልማትን ቀዳሚ ምርጫ በማድረግ እየሠራ መኾኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታውቋል፡፡

በ2015/16 የምርት ዘመን በተፈጠረው የዝናብ እጥረት ምክንያት ድርቅ ከተከሰተባቸው የዋግ ኽምራ አካባቢዎች አንዱ የዝቋላ ወረዳ ነው። በዝቋላ ወረዳ ወንዞችን በመጥለፍ በበጋ መስኖ ልማት ተጠቃሚ መኾናቸውን የዝቋላ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።

አርሶ አደር ብርሃኑ በለጠ የደብረ ፀሐይ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ የተከዜ ወንዝን በመጥለፍ አምስት ሄክታር መሬት በቆሎ በክላስተር እያለሙ እንደኾነ ገልጸዋል። በቀይ ሽንኩርት ልማት ከአሁን በፊት እስከ 300 ሺህ ብር ድረስ እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩ በዘንድሮው ዓመትም አምስት ሄክታር መሬት በቀይ ሽንኩርት ማልማታቸውን ነው የገለጹት።

መንግሥት በውድ ዋጋም ቢኾን የነዳጅ እና የምርጥ ዘር ግብዓት እያቀረበልን ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ በቀጣይም የኬሚካል ርጭት እና የነዳጅ አቅርቦቱ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ መንግሥትን ጠይቀዋል።

ሌላኛው አርሶ አደር እነተወ ኪዴ በበኩላቸው በማሽላ ዘር በመጀመሪያ ዙር 20 ኩንታል እንዳገኙ ገልጸዋል። በበጋ መስኖ የበቆሎ ክላስተር ልማትም ከስምንት ሄክታር መሬት 80 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እያለሙ እንደኾነ ገልጸዋል።

የወረዳው ሰብል ልማት ባለሙያ መኮነን ንጉሤ በበኩላቸው በወረዳው 240 ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት አቅደን 257 ሄክታር በማልማት ከእቅዳችን በላይ እየፈጸምን እንገኛለን ብለዋል።

ወረዳው የምርጥ ዘር፣ የማዳበሪያ እና ለጄኔሬተሮች ነዳጅ ለአርሶ አደሮቹ ከወቅቱ ገበያ ቀንሶ እያቀረበ እንደኾነም አቶ መኮነን ገልጸዋል። የኬሚካል ርጭቱንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩን እንፈታዋለን ብለዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አትክልት ፍራፍሬ መስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ ደሳለኝ አዳነ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በዞኑ የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የበጋ መስኖ ልማትን ቀዳሚ ምርጫ በማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል።

በአንደኛ ዙር የበጋ መስኖ ልማት እንደ ብሔረሰብ አስተዳደር 6 ሺህ 940 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ 5 ሺህ 247 ሄክታሩን እስከ አሁን አልምተናል ነው ያሉት።

የምርጥ ዘር፣ የውኃ መሳቢያ ሞተሮች፣ የማዳበሪያ አቅርቦት እና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ በኩል መምሪያው ከወረዳ የግብርና ሴክተሮች ጋር በጥምረት እየሠራ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም መሰል ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ የህልውና ጉዳይ መኾኑን የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ይማም ገለጹ፡፡
Next article“ከአፍሪካ መዲና እስከ ዓለም የሚደርሰው የዲፕሎማሲ ሳምንት ነገ በይፋ ይከፈታል” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር