የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ የህልውና ጉዳይ መኾኑን የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ይማም ገለጹ፡፡

33

ደሴ: ጥር 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን የ2016 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደሴ ዙሪያ ወረዳ በ029 ቀበሌ በአውዝና 2 ተፋሰስ ዛሬ ተካሂዷል።

በተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የዞን እና የወረዳ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት በደቡብ ወሎ ዞን 1 ሺህ 416 ተፈሰሶች ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ የሚሠራ ሲኾን 9 ተፋሰሰች በዚህ ዓመት የሚጀመሩ ናቸው ተብሏል፡፡

ከ58 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራው እንደሚሸፍን ተገልጿል፡፡ ከጥር 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ በ520 ቀበሌዎች ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራውን ለማከናወን የትግበራ ሥራ ተጀምሯል።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ እና አጠቃቀም ቡድን መሪ መገርሳ ተሾመ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ ምርታማነትን ለማሳደግ መሠረታዊ ጉዳይ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡

ቡድን መሪው የተፋሰስ ልማት ሥራው አርሶ አደሮችን እና አመራሮችን በማስተባበር በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለማጠናቀቅ ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ይማም በበኩላቸው “የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ የህልውና ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡ በወረዳው ያለውን መልካም ተሞክሮ በማስፋት የተፋሰስ ልማት ሥራውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ባሉ 20 ወረዳዎች ሥር በሚገኙ ከ520 በላይ በሚኾኑ ቀበሌዎች በቅድመ ዝግጅት ሥራው የሚሠራ የሰው ኃይል ልየታ፣ የልማት መሣሪያዎችን የማዘጋጀት እና ቀያሽ አርሶ አደሮችን የመመልመል ሥራዎች መሠራታቸው ተነግሯል፡፡

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የተፋሰስ ልማት ሥራውን በዞኑ ባሉ 20 ወረዳዎች በተጠናከረ መልኩ እስከ ጥር 30/2016 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉ ተነግሯል።

ዘጋቢ፡- ደምስ አረጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”ቱሪዝም ያለውን ጠቀሜታ ተረድተን በትኩረት እየሠራን ነው” የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ
Next articleድርቁን ለመቋቋም የበጋ መስኖ ልማትን ቀዳሚ ምርጫ በማድረግ እየሠራ መኾኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ፡፡