”ቱሪዝም ያለውን ጠቀሜታ ተረድተን በትኩረት እየሠራን ነው” የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ

23

ባሕር ዳር: ጥር 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላትን በማክበርና በማስፋፋት ባሕር ዳርን የጎብኝዎች ኹነኛ መዳረሻ ለማድረግ ከተማ አሥተዳደሩ የ”ጥርን በባሕር ዳር” ንቅናቄ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል። በመድረኩ የባሕር ዳርን የቱሪዝም ሃብት ማልማት በሚቻልበት ኹኔታዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው “ጥርን በባሕር ዳር” የከተማዋ አንድ መገለጫ እየኾነ እንደመጣ ገልጸዋል። በባሕር ዳር ጥርን ሙሉ የተለያዩ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ እና ኪነ ጥበባዊ በዓላት እና ትዕይንቶች እንደሚከበሩ እና እንደሚስተናገዱ ነው ኀላፊው የገለጹት።

ባለፉት ዓመታት በዓሉ በመከበሩ በርካታ የውስጥ እና የውጪ ጎብኝዎች ባሕር ዳርን እንዲጎበኟት አስችሏል ያሉት አቶ ጋሻው በዓሉን ማክበራችን ጎብኝዎች ብዙ ጊዜያቸውን በከተማዋ እንዲያሳልፉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ይህም ለሆቴሎች መነቃቃትን፣ ለባሕላዊ አልባሳት እና ቁሳቁሶች ገበያን፣ ለቱሪስት መዳረሻዎች መታወቅን ፈጥሯል ብለዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ከተማዋን እና የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ የቱሪስት መስህቦችን በማስተዋወቅ በዘርፉ ተጠቃሚ ለመኾን ያለመ መኾኑን ገልጸዋል። የከተማዋን ሰላም በማስከበር ቱሪስት ወደ ከተማዋ እንዲመጣና እንዲቆይም እየተሠራ ነው ብለዋል።

የተቀዛቀዘው ምጣኔ ሃብት እንዲነቃቃ እና ባሕር ዳርም በቱሪዝም ተጠቃሚ እንድትኾን የሰላሙን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው ብለዋል። የከተማዋ ነዋሪዎችም አካባቢው ሰላም እንዲኾን እና በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ እንዲተባበሩ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) ቱሪዝም ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ቱሪዝም ያለውን ጠቀሜታ ተረድተን በትኩረት እየሠራን ነው፤ ባሕር ዳር ከተማንም ለቱሪዝም ባላት አቅም ልክ መስህብ በማድረግ ተጠቃሚ እንድትኾን እየሠራን ነው ብለዋል። ያሏትን የቱሪስት መስህቦችም በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በሂደት ላይ መኾኑንም አስረድተዋል።

በክልሉ ቅርሶችን እና ሙዚየሞችን የማደስ እና የመገንባት፣ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን የመገንባት እና የማስተዋወቅ ሥራዎችም እየተሠሩ መኾኑንም ጠቁመዋል። ባሕር ዳርን ዓመቱን በሙሉ ቱሪስት እንዲጎበኛት በማድረግ ባሕል፣ ታሪክ እና እሴትን ለማጎልበት እና ለማስቀጠል ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር ተባብረው እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

የራህናይል ሆቴል የምግብ እና መጠጥ ክፍል ኀላፊ መለሰ ቀለሙ ጥርን በባሕር ዳር ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን በምቾት አስተናግዶ ለመሸኘት ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል። ከሀገር ውስጥም ከውጪም የሚመጡ እንግዶችን ተቀብለን በማስተናገድ በከተማዋ እንዲቆዩ እና ሌላ ጊዜም እንዲመጡ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።

በባሕር ዳር ከተማ በጥር በሙሉ የተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት ክዋኔዎችን እንዲሁም ትዕይንቶችን በመፈጸም የከተማዋን መስህቦች የሚያስተዋውቁ ሥራዎች እንደሚሠሩ በውይይቱ ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የክልሉ መንግሥት የሰብዓዊ አያያዝ ላይ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሠርቷል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleየተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ የህልውና ጉዳይ መኾኑን የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ይማም ገለጹ፡፡