“የክልሉ መንግሥት የሰብዓዊ አያያዝ ላይ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሠርቷል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

22

ባሕር ዳር: ጥር 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ጋር ተወያይተዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድም ተጠርጥረው የተያዙ ዜጎች የሰብዓዊ አያያዝ በጥሩ ሁኔታ ላይ መኾኑን አስታውቋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ሠብሣቢ አዝመራ አንዴሞ የክልሉ የሰላም ኹኔታ እየተረጋጋ መኾኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል። መርማሪ ቦርዱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወረ እየገመገመ መኾኑንም አንስተዋል።

የመርማሪ ቦርዱ ሥራ በዜጎች ላይ አላስፈላጊ የሰብዓዊ ጥሰት እንዳይኖር መከታተል መኾኑንም ገልጸዋል። ምልከታ በተካሄደበት አካባቢ የተያዙ ሰዎች በጥሩ ኹኔታ ላይ መኾናቸውንም አመላክተዋል።

ተጠርጥረው የተያዙ ዜጎች የተሀድሶ ሥልጠና እየተሰጡ ወደ ማኅበረሰቡ መመለሳቸው በበጎ የሚታይ መኾኑንም አመላክተዋል። የክልሉ መንግሥት የሰላም ጥሪ ማቅረቡ መልካም አጋጣሚ መኾኑንም ገልጸዋል። ከሕዝብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች በቂም በቀል የሚታሰሩ ወገኖች አሉ የሚል ጥያቄ መነሳቱንም አንስተዋል። መንግሥት ከሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን መመርመር እና ማስተካከል ይገባዋል ብለዋል።

በተጠርጣሪዎች ላይ የሚደረገውን ምርመራ ማፍጠን እንደሚገባም ገልጸዋል። ሕዝቡ በየትኛውም አማራጭ ይሁን ሰላም እንደሚፈልግ ማንሳቱንም አመላክተዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ነጃት ግርማ (ዶ.ር) መንግሥት ለቦርዱ ሥራ እያደረገው ያለው ቅንነት የሚመሠገን መኾኑንም ተናግረዋል። የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጥሩ መኾኑንም አመላክተዋል። ከምርመራ ግልፀኝነት ላይ የሚነሳውን ጥያቄም መፍታት እንደሚገባ ነው የገለጹት። በተደረጉ ውይይቶች ሕዝቡ ሰላም ፈላጊ መኾኑን፤ ከግጭቱ መማሩን እና ለጥያቄዎቹም መልስ የሚፈልግ መኾኑንም መመልከታቸውን አንስተዋል።

የመርማሪ ቢርዱ አባላት የተጠርጣሪዎች አያያዝ የሀገሪቱን የፍትሕ ሥርዓት መሻሻልን የሚያሳይ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ምን እየሠራ እንደኾነም ጠይቀዋል። የክልሉ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ በእስር ላይ የቆዩ ዜጎች እጣ ፋንታ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄም ተነስቷል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ በሕግ ማስከበሩ ሂደት ተሳታፊ እነማን ናቸው የሚል ልየታ መሠራቱን ገልጸዋል። በግጭት ውስጥ የነበሩ ኀይሎችን አሰላለፍ ልየታ ማድረጋቸውንም አንስተዋል። በተዛባ ቅስቀሳ እና በመንግሥት በኩል የተዛባ የፖለቲካ አሠራር የተደናገረ መኖሩን ገልጸዋል። የተደናገረውን የኅብረተሰብ ክፍል ጉዳት እንዳይደርስበት መሠራቱንም አመላክተዋል።

በአማራ ክልል ያለው ችግር የተፈጠረው በዋናነት ለዘመናት በተነገረው ሐሰተኛ ትርክት መኾኑንም አንስተዋል። ችግርን በውስጥ አቅም መፍታት ካልቻልን ራስን ወደ መብላት እና ሀገርን ወደ ማተራመስ እንደሚዘልቅም ነው ያስረዱት።

በክልሉ ከጥቂት ወረዳዎች ውጭ ሌሎች አካባቢዎች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መኾናቸውንም ገልጸዋል። በመረጃ ክፍተት ተደናግሮ የነበረው የኅብረተሰብ ክፍል በተሠራው ሥራ በተግባር ከመሳተፍ እየራቀ መኾኑንም ተናግረዋል። ሕዝቡ የታጠቁ ኀይሎችን ያልተገባ ድርጊት እያየ እየራቃቸው መኾኑንም አንስተዋል።

የመንግሥት መዋቅር እስከታችኛው ድረስ እየተዘረጋ መኾኑንም ገልጸዋል። አሁን ላይ በተወሰደው እርምጃ ከፊት ለፊት ውጊያ ወደ ሽምቅ፣ ከሽምቅ ወደ ሽብር ተግባር መውረዱንም አንስተዋል።

የክልሉ መንግሥት የሰብዓዊ አያያዝ ላይ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሠርቷል ብለዋል። ከሰብዓዊ አያያዝ ጋር ስህተቶች ካሉም እየተከታተልን እናስተካክላለን ነው ያሉት። በሰብዓዊ አያያዝ ላይ ስህተት መሥራት እንደማያስፈልግም ገልጸዋል።

ግጭቱን እንደ ገቢ ማስገኛ የሚጠቀሙ ኀይሎች መኖራቸውን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ከተሞች ላይ ግጭት በመፍጠር ገቢ ለማግኘት የሚደረጉ ሙከራዎች መኖራቸውን አንስተዋል።

በተደጋጋሚ ከሕዝብ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ መንግሥት ለውይይት በሩ ክፍት መኾኑንም አመላክተዋል። ከአሁን ቀደም ከሕዝብ ጋር ብቻ ሳይኾን ከታጠቁ ኀይሎች ጋር ውይይት መደረጉንም አስታውሰዋል። የክልሉ መንግሥት ለውይይት በሩ ዝግ ነው የሚሉ ክሶች ተገቢ አለመኾናቸውን አንስተዋል።

የተደረገው የሰላም ጥሪ በሕገ መንግሥቱ ይቅርታ ከማይደረግላቸው ወንጀሎች ውጭ ከዚህ ቀደም የነበሩ ወንጀሎችን ይቅርታ እንደሚያሰጥም አንስተዋል። እኛ ያቀረብነው የሰላም ጥሪ እንጂ እጅ ስጡ አላልንም፤ የክልሉ መንግሥት እጅ ስጡ አለ እየተባለ የሚናፈሰው አካሄድ ልክ አይደለም ብለዋል። የክልሉ መንግሥት በሰላም ለሚገቡ ኀይሎች ትጥቃቸውን ሕጋዊ እያደረገ እንደሚሰጥም አንስተዋል። ለሰላም እጁን ከዘረጋ ከየትኛውም ኀይል ጋር ለውይይት ዝግጁ ነንም ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እንዲፈቱ የሚታገሉትን ነውር ነው አንልም፤ ነውር የሚኾነው ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚደረጉ ሕገወጥ አካሄዶችን ነው ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ። ትክክለኛ ጥያቄ ከያዘ አካል ጋር ብቻ ሳይኾን ትክክለኛ ጥያቄ ካልያዘ አካል ጋርም ለመወያየት እና ችግሮችን በሰላም ለመፍታት መንግሥት ዝግጁ ነው ብለዋል።

የሰላም ጥሪው በክልሉ በርካታ ጥቅሞች እና ለውጦችን ማምጣቱን ነው የተናገሩት። በሰላም ጥሪው ከ6 ሺህ በላይ የቀድሞ የልዩ ኀይል አባላት መግባታቸውንም ገልጸዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ኀይሎችም እየገቡ መኾናቸውን ነው ያነሱት። በሰላም የሚገቡ ኀይሎች ቁጥር ከቀን ቀን እየጨመረ መኾኑንም አስታውቀዋል። ይህም ለክልሉ ሕዝብ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ሥራ የተሻለ ተሞክሮ እንዳለ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ገለጹ፡፡
Next article”ቱሪዝም ያለውን ጠቀሜታ ተረድተን በትኩረት እየሠራን ነው” የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ