
እንጅባራ: ጥር 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በወቅታዊ ሰላም እና ፀጥታ ዙሪያ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር በእጅባራ ከተማ መክረዋል።
“አብሮነታችንን በማጠናከር ሰላማችንን እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው በዚሁ የምክክር መድረክ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የፀጥታ መዋቅሩ ከማኅብረሰቡ ጋር በመቀናጀት በሠራው የተጠናከረ ሥራ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች ሰላማዊ ሁኔታ እንደሚታይባቸው ገልጸዋል።
አለመረጋጋት የሚስተዋልባቸውን አካባቢዎች ወደ ቀድሞ ሰላማቸው ለመመለስ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል። የብሔረሰብ አሥተዳደሩ በጊዜያዊ ችግሮች ሳይበገር የዳበረ አብሮ የመኖር ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባሕሉን በመጠቀም አካባቢው ወደ ቀድሞ ሰላሙ እንዲመለስ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም ዋና አሥተዳዳሪው አሳስበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ተቻችለው እና ተከባብረው ዘመናትን በጋራ የተሻገሩ ሕዝቦችን ለማለያየት እና ግጭት ውስጥ ለመክተት የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።
ሕዝብን ለቅሬታ የዳረጉ የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ሊፈቱ እንደሚገባም ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!