
ጎንደር: ጥር 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር በማራኪ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች የአካባቢያቸውን የሰላም ኹኔታ አስመልክተው ሀሳባቸውን ለአሚኮ አጋርተዋል።
የክፍለ ከተማው ነዋሪ አቶ ገብሬ ሞገስ እና አቶ ዘውዱ ኀይሌ እንዳሉት ሰላም የሁሉም መሰረት በመኾኑ ሰላምን በማስቀደም ችግሮችን በተገቢው መንገድ መፍታት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
መንግሥት ብቻውን ሰላምን ለማረጋገጥ በሚሠራው ሥራ የሚፈለገው ሰላም ሊመጣ ስለማይችል ሁሉም ማኅበረሰብ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ያሉ ችግሮችን በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ መፍታት አስፈላጊ መኾኑንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ተቋማትን በባለቤትነት ስሜት ለመጠበቅ እና ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ማኅበረሰቡ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ እየሠራ መኾኑን የማራኪ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ኀይለ ሚካኤል አለባቸው ገልጸዋል።
በክፍለ ከተማው ተከስቶ የነበረውን ችግር በአጭር ጊዜ ወደ ነበረበት ሰላም ለመመለስ የማኅበረሰቡ አበርክቶ የጎላ መኾኑንም ሥራ አሥፈፃሚው ተናግረዋል። በክፍለ ከተማው ወቅታዊ የሰላም ኹኔታን አስመልክቶ ከነዋሪዎች ጋር የውይይት መድረክም ተካሂዷል።
ዘጋቢ፡- ቃልኪዳን ኃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!