
ባሕር ዳር: ጥር 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2016 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ከ240 በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በላሊበላ በቦታው ተገኝተው መታደማቸውን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተከበረው የዘንድሮው የልደት በዓል የክልሉን አሁናዊ ገጽታ በበጎ ጎኑ ያመላከተ እንደነበር የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እና የቅዱስ ላሊበላ ዓመታዊ ክብረ በዓል በተለየ ሁኔታ በሚከበርባት ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ላሊበላ በዓሉ ፍጹም ሰላማዊ ኾኖ ተጠናቋል ተብሏል፡፡ ከ240 በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች እና ከ512 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ምዕመናን ልደትን በላሊበላ መታደማቸውን ቢሮው አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ በየዓመቱ በተለየ ድምቀት እና ውበት የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በጥንታዊቷ ላሊበላ የተለየ ድባብ አለው፡፡ ከኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በተጨማሪ የቅዱስ ላሊበላን ዓመታዊ ክብረ በዓል የምታስተናግደው የላሊበላ ከተማ ስኬታማ መስተንግዶን አድርጋለች ተብሏል፡፡
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አበበ እምቢያለ የዘንድሮው የልደት ክብረ በዓል ስኬታማ ነበር ብለዋል፡፡ በዓሉ ክልሉ ከከረመበት ውስብስብ የሰላም እጦት አንጻር ሲታይ የክልሉን አሁናዊ ገጽታ በበጎ ጎኑ ለቀሪው ዓለም ያመላከተ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት ከነበረው ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ክስተት በኋላ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ላለፉት ዓመታት ተጎድቶ ቆይቶ ነበር ያሉት አቶ አበበ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኋላም በተደጋጋሚ በአካባቢው የተፈጠረው የሰላም እጦት ዘርፉን ክፉኛ ጎድቶት ቆይቷል ብለዋል፡፡
ላለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እና በክልሉ ለወራት የቀጠለው የሰላም እጦት ህልውናዋ በቱሪዝም ገቢ ላይ ለተመሰረተው የላሊበላ ከተማ ፈታኝ ጊዜ እንደነበር አንስተዋል፡፡ የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር፣ የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳደር እና የክልሉ መንግሥት ለበዓሉ በነበራቸው የተቀናጀ ቅድመ ዝግጅት የልደት በዓል በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ ተስፋ ሰጭ እና ስኬታማ ኾኖ ተጠናቋል ነው ያሉት፡፡
የልደት በዓልን በላሊበላ ለመታደም 242 የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ተገኝተዋል ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው 512 ሺህ የሀገር ውስጥ ምዕመናንም ከአራቱም አቅጣጫ በጉዞ ማኅበራቸው አማካኝነት በሰላም ገብተው እና በዓሉን በስኬት አክብረው ተመልሰዋል ብለዋል፡፡
በዓሉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም መጠናቀቁ በቀጣይ ለሚከበሩ ክብረ በዓላት እና ለቱሪዝም እንቅስቀሴው ተስፋ የሰጠ ከመኾኑ በተጨማሪ የክልሉን አሁናዊ ሁኔታ በበጎ ጎኑ ያሳየ እንደ ነበር ጠቁመዋል፡፡ በጥር የሚከበሩ ቀሪ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት ስኬታማ ኾነው እንዲጠናቀቁ ልምድ የተገኘበት እንደኾነም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!