የተቀናጀ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

35

ባሕር ዳር: ጥር 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የኢፌዴሪ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንና በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን ወቅታዊ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በተመለከተ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

በመግለጫውም የኢትዮጵያ መንግሥት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የግብርና ምርታማነትን በማሳደግና የምግብ ዋስትና መረጋገጥ ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑ ተገልጿል። ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ እየተከሰተ የሚገኘው ድርቅ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል የሁሉንም አጋር አካላት ድጋፍና ትብብር እንደሚጠይቅ በመግለጫው ተመላክቷል።

መግለጫው አክሎም በአፋር፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ ፣ደቡብ ፣ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በድርቅ የተጠቁ አካባቢዎች 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደስፈልጋቸው አስታውቋል።

ድርቁን ተከትሎ ካጋጠመው የምግብ እጥረት ባለፈ በነዚህ አካባቢዎች እንደ ወባ፣ ኩፍኝና ኮሌራ ያሉ በሽታዎች መከሰትን ጨምሮ በቀንድ ከብቶች ላይም ጉዳት እየደረሰ መሆኑ ተገልጿል።

ያለው ስር የሰደደ የሃብት ውስንነት እንዳለ ኾኖ ድጋፎቹን በሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ለማዳረስ በአንዳንድ ኪስ አካባቢዎች የሚያጋጥመው የጸጥታ ችግር የሰብዓዊ እርዳታ የማከፋፈሉን ሥራ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳረፉም መግለጫው አመላክቷል።

ይሄም ኾኖ መንግሥትና የረድኤት ድርጅቶች በአብዛኛው በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ሰብዓዊ እርዳታ ማዳረስ መቻላቸውን አስታውቋል። ከሦስት ዙር በላይ በተደረገ ድጋፍ የማዳረስ ጥረትም በመንግሥት ቢያንስ ለ 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ መቻሉ ተገልጿል።

በታኅሳሥ ወር አጋማሽ እንደገና በተጀመረው የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የሌሎች አጋር አካላት እገዛ በአማራ ፤በትግራይ፣ በሶማሌና በአፋር ክልሎች በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች ወደ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል።

ይህ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የቅድሚያ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ በጥር ወርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጫው አመላክቷል። ለጋሽ አካላትም ይሄንኑ እንስቃሴ ለማገዝ ትኩረት እንዲሰጡ በመግለጫው ጥሪ የቀረበ ሲሆን ወቅቱን የጠበቀ ምላሽ በገንዘብ ድጋፍና በሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑም ተመላክቷል።

በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ተደራሽ ለማድረግም የተቀናጀ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት አስፈላጊ መሆኑም ተገልጿል። መንግሥትና የረድኤት ድርጅቶች ሰብዓዊ እርዳታ በማድረስ በኩል ያላቸውን ልምድና የተጠናከረ የባለሙያ ስብስብ ለዚሁ ተግባር ለማዋል ዝግጁ መሆናቸውም መግለጫው አመልክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ መጻዒ ፈተና!
Next articleከ240 በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በላሊበላ ተገኝተው የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል መታደማቸውን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።