
ባሕር ዳር: ጥር 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ እየፈተኑት ከሚገኙ ምክንያቶች መካከል የመጤ አረም መስፋፋት አንዱ ነው። በእርሻ መሬት ላይ የሚታዩ አረሞች መደበኛ፣ አደገኛ፣ መጤ እና ወራሪ ተብለው ይመደባሉ፡፡ መደበኛ አረም እንክብካቤ ባልተደረገለት ሰብል ውስጥ በመስፋፋት በምርታማነት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነው።
አሁን ላይ የግብርና ምርታማነትን እየተፈታተኑት ከሚገኙት ችግሮች መካከል አንዱ አደገኛ፣ መጤ እና ወራሪ አረም ዋነኛው ነው። አረሙ በዓይነት፣ በመጠን እና በተስፋፊነት ፍጥነቱ ከፍተኛ በመኾኑ በምርታማነት ላይ የሚያደርሰው ጉዳትም በዚያው መጠን ከፍተኛ እንደኾነ የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ እና የአየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር አወቀ ይታይ ገልጸዋል።
አረሙ አሁን ላይ እንደ ጣና ካሉ የውኃማ አካላት ባለፈ በእርሻ እና በግጦሽ ቦታዎች ጭምር እየተስፋፋ ይገኛል ተብሏል። አረሙ ይበልጥ በምሥራቁ የክልሉ ክፍል በስፋት ተስፋፍቶ የሚገኝ ቢኾንም አሁን ላይ ወደ ምዕራቡ የክልሉ ክፍልም አድማሱን እያሰፋ መኾኑን ዳይሬክተሩ ገልጸውልናል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የአረም ዝርያዎች መኖራቸውን ያነሱት ዳይሬክተሩ አሁን ላይ 12 አደገኛ የአረም ዝርያዎች በአማራ ክልል ጉዳት እያደረሱ መኾኑን ነው ዳይሬክተሩ የነገሩን፡፡
በተለይም ደግሞ የአረም ዝርያዎቹ መስፋፋት በግብርናው ምርታማነት ላይ የመጠን እና የጥራት ማጓደል እያስከተሉ ይገኛሉ። አቀንጭራ የተባለው አደገኛ አረም 65 በመቶ፣ የቅንጨ አረም ደግሞ 15 በመቶ የምርት መቀነስ እንደሚያስከትል ጥናቶች እንደሚያሳዩ ለአብነት አንስተዋል።
አረሞቹ ድርቅ እና ውርጭን የመቋቋም አቅማቸው ከፍተኛ በመኾኑ እጽዋት በቀላሉ እንዳይራቡ፣ እንዳይለመልሙ እና ምርት እንዳይሰጡ የማድረግ አቅማቸው ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡ የግጦሽ መሬትን ያመናምናሉ፤ አረሙን ከብቶች በሚመገቡበት ወቅት የወተት፣ የሥጋ ጣዕም እና ጥራት መጓደል ያመጣሉ፡፡ የማር ምርትን ጣዕም ይቀይራል፡፡
አርሶ አደሮች በሚያርሙበት ወቅት የቆዳ ማሳከክ፣ ማበጥ፣ መሰንጠቅ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ሽታ ስላላቸው ለአስም እና መሰል ህመሞች እንደሚያጋልጡ ገልጸዋል። አረሙን ለመከላከልም ከፍተኛ ወጭ እና ጉልበት ያስወጣል፡፡ ለአካባቢ ብክለትም አስተዋጽኦአቸው ከፍተኛ መኾኑን ነግረውናል።
መጤ አረሞቹ በእንስሳት፣ በወራጅ ውኃ፣ የከብቶች ፍግ ለኮምፖስት ሥራ በሚውልበት ወቅት እና በመሳሰሉ አስተላላፊ መንገዶች በቀላሉ ይተላለፋሉ። በመኾኑም በኮምፖስት ዝግጅት ወቅት በደንብ እንዲብላላ ማድረግ፣ የእርሻ መሳሪያዎች ከቦታ ቦታ በሚጓጓዙበት ወቅት በተገቢ መንገድ ማጽዳት እና የመሳሰሉ የቅድመ መከላከል ሥራ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም መክረዋል።
አረሙ ከተከሰተ በኋላ ደግሞ በእጅ እና በማሽን ማረም፣ የግብርና እና አካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎችን በማማከር ኬሚካል መጠቀም ይገባል ነው ያሉት፡፡ ከዚህ ባለፈ በረጅም ጊዜ በምርምር እና በጥናት የተደገፈ ሥነ ሕይወታዊ የመከላከያ ዘዴ ላይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና የምርምር ማዕከላት ከወዲሁ ሊሠሩ እንደሚገባ መክረዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ተስፋፊ አረሞችን ከ2010 እስከ 2030 ዓ.ም ለመከላከል በፌዴራል ደረጃ ስትራቴጅ ወጥቷል። ባለፉት ዓመታት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት የተሠሩ ጅምር ሥራዎች ቢኖሩም ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ አለመኾኑን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ አርሶ አደሮች መሬታቸውን ከመጤ አረም እንዲከላከሉ የሚያስችል ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ባለሥልጣኑ ግፊት እያደረገ መኾኑንም አስረድተዋል፡፡ በክልሉ በአደገኛ እና መጤ አረም የተወረረውን የመሬት ሽፋን ለማወቅ ጥናት እየተደረገ መኾኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጉዳዩ ይበልጥ የሚመለከታቸው ተቋማት አሁንም ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡ አርሶ አደሮችም ንጹህ ዘር መጠቀም እና አረሙን ከጅምሩ ማረም ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፣ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!