የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃን ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እንደሚሠራ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

38

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃን ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እንደሚሠራ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በጥላቻ ንግግር እና በሐሰተኛ መረጃ መከላከያ መንገዶች ዙሪያ ለበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እና የሥራ ኀላፊዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጥቷል።

በሥልጠናው ላይ የተገኙት የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ በባለሥልጣኑ ተመዝግበው በሥራ ላይ የሚገኙ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎች በጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት መከላከል እና መቆጣጠር ላይ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። እርስ በእርስ ቁጥጥርን በማጠናከር ረገድ ግንዛቢያቸውን እንዲያዳብሩ ለማስቻል የስልጠና መድረኩ እንደተዘጋጀም ተናግረዋል፡፡

አቶ ግዛው ባለሥልጣኑ ከበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ማኅበር ጋር ወደፊት የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃን ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ይሠራል ብለዋል፡፡ ሥልጠናው የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ምንነት፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ባሕሪያት፣ እውነትን ማጣራት፣ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃን በመከላከል ረገድ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ሚና እንዲኹም የእርስ በርስ ቁጥጥር ሂደት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነበር፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃን በመከላከል ረገድ ከባለሥልጣኑ እና ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር በትጋት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ማኅበሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

በሀገራችን በአሁኑ ሰዓት በባለሥልጣኑ ተመዝግበው ፈቃድ የወሰዱ 63 የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ይገኛሉ። በማንኛውም ሁኔታ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ሲመለከቱ በ9192 ነጻ የስልክ መስመር ደውሎ ማሳወቅ እንደሚቻልም ባለሥልጣኑ አስገንዝቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በብሔረሰብ አሥተዳደሩ እየተሠራ ያለው የሕግ ማስከበር ተግባር የሚበረታታ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን
Next articleየግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ መጻዒ ፈተና!