
አዲስ አበባ: ታኅሳስ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ30 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ በባሕር ዳር፣ በሃዋሳ፣ በአዳማ እና በሶዶ ከተሞች የከተማ መሬት አያያዝ እና የማዘመን ተግባር ሊከናወን እንደኾነ ተገለጸ፡፡
የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እና የኮሪያው ዋቩስ ድርጅት የከተማ መሬት አያያዝ እና የማዘመን ተግባርን በኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የስምምነት ውል ተፈራርመዋል፡፡
ከኮሪያው ኤግዚም ባንክ በተገኘ የ30 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለሚተገበረው የከተማ ልማት ዘርፍ የኮሪያው ዋቩስ የሶፍትዌር አበልፃጊ ድርጅት ዘመናዊ የመሬት መረጃ ምዝገባ እና አደረጃጀት ላይ ለመሥራት ስምምነቱን ተፈራርሟል።
በስምምነቱ ላይ የተገኙት የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በቀጣይ የሚተገበረው የዛሬው ስምምነት ላልዘመነው፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግር ለኾነው የመሬት አያያዝ መፍትሄ ይሰጣል ብለዋል። በስምምነቱ መሰረትም በባሕር ዳር፣ በሃዋሳ፣ በአዳማ እና በሶዶ ከተሞች ተግባራዊ እንደሚደረግም ተገልጿል።
በሥምምነቱ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዋቩስ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኪም ሀክ ሰንግ ሥራው ለኢትዮጵያ የተሻለ የወደፊት ሁኔታ ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል። ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የመሬት መረጃ አሥተዳደር ሥርዓትን ለመገንባት ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር ንቁ ትብብር በማድረግ እንደሚሠሩም አስረድተዋል፡፡
በሥራውም የኢትዮጵያን የመሬት አሥተዳደር ቅልጥፍናን ለማሳደግ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል። ስምምነቱ በሕዝብ አገልግሎት ውስጥ አዳዲስ ማሻሻያዎችን ይዞም ይመጣል ተብሎም ይጠበቃል።
“ሥነ ሥርዓቱ ውል ብቻ ሳይኾን መተማመን እና መከባበርን ለማጠናከር እንደ ዕድል ኾኖ ያገለግላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ነው ያሉት፡፡ ዋና ሥራ አሥፈፃሚው የተሳካ ውጤት ለማስመዝገብ እና የከተሞች ዕድገት የማዕዘን ድንጋይ ለመኾን በጋራ ለመሥራት እንደሚተጉ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!