በአማራ ክልል 61 የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ መኾኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር አስታወቀ፡፡

38

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚሠሩ የመንገድ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በባሕር ዳር ከተማ እየተገመገመ ነው።

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም የተመለከተ ግምገማ እና ውይይት የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር አመራሮች የውይይቱ ተሳታፊዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር በአማራ ክልል በአጠቃላይ 61 የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶችን እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል። የመንገዶቹ አጠቃላይ ድምር ርዝማኔ 3 ሺህ 658 ኪሎ ሜትር ነው። የመንገድ ግንባታዎቹ በ97 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነቡ ስለመኾናቸው የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ገልጿል።

በአዲስ ከሚሠሩ መንገዶች በተጨማሪ 3 ሺህ 664 ኪሎ ሜትር ነባር መንገዶችም እየተጠገኑ መኾኑ ተጠቁሟል። ከ2 ቢሊዮን 166 ሚሊዮን 529 ሺህ በላይ ብር ለመንገዶች ጥገና ተመድቦ እየተሠራ ስለመኾኑም ተነግሯል።

ውይይቱ በክልሉ የሚከናወኑ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ወደ ጠንካራ አፈጻጸም ለማስገባት እና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ ስለመኾኑ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ግብርና የልማት እና የእድገት የጀርባ አጥንት በመኾኑ ሰላም ይፈልጋል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
Next article“የልብ ህሙማን ህፃናት ወር” ተብሎ በተሰየመው የጥር ወር ኢትዩ ቴሌኮም የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራዎችን አንደሚያከናውን አስታወቀ።