
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2016 ዓ.ም የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ላይ ያተኮረ ክልላዊ የውይይት መድረክ በደሴ ከተማ እያካሄደ ነው።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራን በአግባቡ ማከናወን ካልተቻለ እንደ ሀገር የሚገጥምን ፈተና መቋቋም እንደማይቻል አስረድተዋል።
ዶክተር ድረስ ባለፉት ዓመታት በክልሉ በተሠሩ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች የክልሉ የደን ሽፋን 15 ነጥብ 7 ከመቶ ደርሷል ነው ያሉት፡፡ የአማራ ሕዝብ ትልቁ ጥያቄ የልማት ጥያቄ ነው ያሉት ኀላፊው “ግብርና የልማት እና እድገት የጀርባ አጥንት በመኾኑ ሰላም ይፈልጋል” ብለዋል፡፡
የግብርናው ዘርፍ ተዋንያን ትኩረታቸው ሰላምን ማስጠበቅ እና ልማት ላይ ሊኾን እንደሚገባም አብራርተዋል፡፡ በውይይት መድረኩ የዞን አሥተዳዳሪዎች፣ የከተማ አሥተዳደር ከንቲባዎች፣ የግብርና ኀላፊዎች እና የተፋሰስ ልማት ባለሙያዎች ተገኝተዋል ።
ዘጋቢ፡- ከድር አሊ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!