ንጉሥም ቅዱስም የኾነው የላሊበላ ልደት እና የእጆቹ ሥራ

24

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለማችን ካሉት አስደማሚ ኪነ ሕንጻዎች መካከል ይመደባል። በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያውም በሥልጣኔ አልባነት ተፈርጆ “ጨለማው አህጉር” በተባለው አፍሪካ ውስጥ መገኘቱ አነጋጋሪነቱ እና አመራማሪነቱ እንደቀጠለ ነው።

ምዕራባውያን የሥልጣኔ አሻራቸው እንዳለበት ማሳመን ባይችሉም በዚያ ዘመን አፍሪካ ውስጥ ተሠራ ብሎ ለመቀበልም ይተናነቃቸዋል። ከግብፅ ፒራሚዶች፣ ከአክሱም ሥልጣኔ፣ ከሜሶፖታሚያ፣ ከባቢሎን፣ ከቻይና እና ከሕንድ ሥልጣኔዎች መዘግየታቸውን መካድ ያልቻሉት አውሮፓውያን የላሊበላንም ጥበብ ማቃለል አልቻሉም።

የኢትዮጵያ ቀደምት ሥልጣኔ፣ መንፈሳዊ ፍልስፍና እና ጥበብ ተንቦግቡጎ የበራባቸው የአክሱም እና የዛጉየ ሥርወ መንግሥታት ሥልጣኔ ለአፍሪካውያን ቀደምት ሥልጣኔም ከማሳያዎች ውስጥ ናቸው።

በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የተቀረጹት የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ኢትዮጵያን ከሰው ዘር መገኛነቷም በተጨማሪ ቀደምት ሥልጣኔ ከነበራቸው ሀገራት ተርታ ያስመድባታል። በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ከአክሱም ወደ ላስታ ተዛውሮ በዛጉዌ ሥርወ መንግሥት በ11 ነገሥታት ለሦስት መቶ ዓመታት ተመርቷል። ከነዚህ ነገሥታት ውስጥ ቅዱስ እና ንጉሥ ኾነው በተከታታይ የነገሡት ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ሐርቤ (ገብረ ማርያም)፣ ቅዱስ ላሊበላ እና ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ የጎላ ታሪክ አላቸው።

በሀገራችን ታዋቂ የቱሪስት መስህብ የኾነውን ታላላቆቹ የላሊበላ 11 ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት የተገነቡትም ቅዱሥ እና ንጉሥ በኾነው ላሊበላ የንግሥና ዘመን በራሱ አናጺ እና ጠራቢነት ጭምር መኾኑ ድርሳናት ይናገራሉ። ፍልፍል ሕንጻዎቹም ቤተ መድኃኒዓለም፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ ደናግል፣ ቤተ መስቀል፣ ቤተ ደብረ ሲና፣ ቤተ ጎለጎታ፣ ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ አባ ሊባኖስ፣ ቤተ መርቆሬዎስ፣ ቤተ ገብርኤል ወሩፋኤል እና ቤተ ጊዮርጊስ ናቸው።

የላሊበላ ድንቅ ሥራ ከሀገር ውስጥ ዜጋ እስከ የዓለም ተመራማሪ ድረስ እያደር አዲስ የሚኾን አስደማሚ ጥበብ የፈሰሰበት ነው። ድንቅ የሚያደርጋቸው ባልተለመደ የኪነ ሕንጻ፣ በመንፈሳዊ ይዘታቸው፣ ኋላ ቀር በተባለ ዘመን፣ ሀገር እና ሕዝብ ውስጥ የተቀረጹ መኾናቸው ነው። ዛሬም ከ800 ዓመት በኋላ “ሥልጡኖቹ” አውሮፓውያን የኪነ ሕንጻዎቹን የጥበብ ምጥቀት እንዲህ ነው ብለው ለመበየን አለመቻላቸው የቅዱስ እና ንጉሥ ላሊበላን ተሰጥኦ ይመሰክራል።

በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተጻፈ የሚነገርለት ”ገድለ ላሊበላ” እንደሚገልጸው ንጉሥ ላሊበላ ሁለተኛዋን እየሩሳሌም በላስታ ለማስገንባት አልሞ ነው ቤተክርስቲያኖቹን መሥራት የጀመረው። የገድለ ላሊበላ ጸሐፊ ስለ ውቅር አቢያተ ክርስቲያኖቹ ረቂቅ ውበት ሲገልጽ “በላሊበላ እጅ የተሠራ ይህ ድንቅ ሥራ በሥጋዊ ሰው የሚቻል አይደለም። የሰማይን ከዋክብት መቁጠርን የቻለ፣ በላሊበላ እጅ የተሠራውን መናገር ይችላል፤ እናም ለማየት የሚፈልግ ካለ ይመልከት። በላሊበላ እጅ የተሠሩትን ሕንጻዎች ይምጣ እና በዓይኖቹ ይመልከት!” በማለት የኪነ ሕንጻዎቹን ውበት እና የጥበብ ጥልቀት ማድነቂያ ቃል እንዳነሰው ይዘረዝራል።

ለስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ የኖረ ፖርቹጋላዊ ቄስ ፍራሲስኮ አልቫሬዝ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጎብኝቶ “ስለነዚህ ሕንጻዎች ከዚህ በላይ መጻፍ አልችልም። ምክንያቱም ከዚህ በላይ ብጽፍ የሚያምኑኝ አይመስለኝም። እስካሁን የጻፍኩትንም እውነት አይደለም ይሉኛል ብዬ እፈራለሁ። እኔ ግን በሃያሉ እግዚአብሔር እምላለሁ የጻፍኩት ሁሉ እውነት ነው! እውነታው እንዲያውም ከዚህም ከጻፍኩት እጅግ የበለጠ ነው። ውሸታም እንዳይሉኝ ግን ትቼዋለሁ።” ማለቱ ይነገራል።

በገድለ ላሊበላ መጽሐፍ የቤተ ክርስቲያናቱ አሠራርም ተገልጿል። “ገብረ መስቀልም (ላሊበላ) ልዩ ልዩ የኾኑ የብረት መሣሪያዎችን አሠራ። ለመጥረብም የተሠራ አለ። ለመፈንቀልም የተበጀ ብረት አለ። ለመፈልፈልም የተሠራ አለ። እነዚህን ቋጥኝ ድንጊያ የመቅደስ ሕንጻ የሚፈጸምባቸውን አሠራ። ገብረ መስቀልም ከዚያን ጊዜ ወዲህ ምድራዊ ሀሳብን፣ ሚስቱንም ደስ ለማሰኘት ፈቃድ ቢኾንም አላሰበም። ሁሉንም በሙሉ መንፈስ ስለ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት አሰበ እንጂ” በማለት ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የድንጋይ ፍልፍል ሕንጻዎችን መሥራት የተለመደ ቢኾንም የላሊበላን ውቅር አቢያተ ክርክቲያናት ግን በአንድ አካባቢ እና ተቀራራቢ ጊዜ የተፈለፈሉ መኾናቸው ልዩ ከሚያደርጋቸው አንዱ ነው። የፈሰሰባቸው ጥበብ፣ ውበታቸው፣ ግዝፈታቸው ሌላው አስደማሚ ባሕሪያቸው ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በ1970 ዓ.ም በሁለተኛው ጉባኤው የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናትን በዓለም ቅርስነት መዝግቧል።
አሁን ድረስ ዓለምን እያስደነቀ ያለውን ኪነ ሕንጻዎች ያነጸው ቅዱስ እና ንጉሥ ላሊበላ የተወለደው በያዝነው ሳምንት ታኅሳሥ 29/1101 ዓ.ም እንደኾነ ድርሳናት ከትበዋል። ንጉሥ ላሊበላ ስሙን ያገኘው ሲወለድ በንቦች ስለተከበበ መኾኑ ይነገራል። ላል ማለት ማር ሲኾን ላሊበላ ማለት ላል ይበላል (ማር ይበላል) ማለት እንደኾነም በድርሳናት ተገልጿል።

በዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የልደት በዓል በሰላም ተጀምሮ በሰላም ተጠናቅቋል” የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር
Next articleፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሶማሌላንድ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጋር ተወያዩ።