
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ እና የቅዱስ ላሊበላ የልደት በዓል በደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ተከብሯል፡፡ በክብረ በዓሉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የውጭ ሀገር ዜጎች እና በርካታ ምዕምናን ተገኝተዋል፡፡
የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወንድምነው ወዳጅ የልደት በዓል ለየት ባለ ገጽታ ተከብሯል ብለዋል፡፡ በዓሉ የተከበረው ክልሉ የሰላም ችግር ውስጥ ባለበት ጊዜ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በዓሉን ለማክበር የተሠራው ሥራ ስኬታማ እንደነኾነም ገልጸዋል፡፡
በዓሉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም በተሰጠው ድርሻ ልክ በብቃት መወጣቱንም አስታውቀዋል፡፡ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በዓሉ በብዙ መልኩ ትርፋማ ነበርም ብለዋል፡፡ በተሠራው የቅንጅት ሥራ በዓሉ በድምቀት ተጀምሮ በድምቀት መጠናቀቁን አንስተዋል፡፡
በዓሉ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓል ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከፖለቲካዊ አስተሳሰብ በመነጠል በልኩ እና በክብሩ እንዲከበር በተሠራው ሥራ በስኬት መከበሩንም ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ሰላሙን የመጠበቅ እና እንግዶችን ከሥጋት ነጻ የማድረግ ሥራ መሥራቱንም አንስተዋል። ወጣቶች እንግዶችን እግር እያጠቡ ከመቀበል ጀምሮ ለእንግዶች የተመቸ ሥራ መሥራታቸውን ነው የተናገሩት።
የሃይማኖት አባቶችም የሚጠበቅባቸውን እና ቤተ ክርስቲያን የምታዝዘውን በብቃት መፈጸማቸውን ገልጸዋል። በዓሉ እንዲሳካ ላደረጉ ሁሉም ምስጋና አቅርበዋል። በዓሉን ለማክበር ወደ ሥፍራው የመጡ እንግዶችም ደስተኞች መኾናቸውን መግለጻቸውን ነው የተናገሩት።
በበዓሉ ላይ ከ240 በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች መታደማቸውንም አስታውቀዋል። ቱሪዝም ለአካባቢው ማኅበረሰብ እስትንፋስ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የተጀመረውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ማስቀጠል ይጠበቃል ብለዋል። እስትንፋስ የኾነው የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲቀጥል ማኅበረሰቡ ሰላሙን መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።
በአጭር ጊዜ ዝግጅት የተሳካ በዓል መከበሩን ነው የተናገሩት። የአማራ ክልል መንግሥት በዓሉ እንዲከበር ላደረገው ሥራ ሁሉ አመስግነዋል። የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ለበዓሉ የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን በመስጠት እና ሌሎች ሥራዎችን በመሥራት ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል። ሌሎች ሚዲየዎችንም አመስግነዋል።
ላሊበላ በረከት እና የኢትዮጵያውያን ኩራት ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለከተማዋ ከቱሪዝም ውጭ ሌላ ሃብት እንደሌላት ገልጸዋል። ብቸኛውን አማራጭ ሰላሙን ጠብቆ መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል። ቱሪዝም በሰላም ምክንያት በመጎዳቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ ለችግር ተጋልጦ መቆየቱንም አንስተዋል። የአካባቢው ብቸኛ ሃብት የኾነውን በዓል መጠበቅ አስፈላጊ ነውም ብለዋል።
መሠረታቸውን በቱሪዝም ላይ ያደረጉ ተቋማት እና ግለሰቦች እንዲጠቀሙ ለሰላም መሥራት ይጠበቃል ብለዋል። የልደት በዓል የሰላም ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ችግሮችን በውይይት በመፍታት ሰላምን ማጽናት ይገባል ነው ያሉት። ችግሮችን በውይይት በመፍታት አንድነትን እያጠናከሩ መሄድ እንደሚገባም አመላክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!