
ባሕርዳር: ታኅሳሥ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 47ኛው የአፍሪካ ኅብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ መደበኛ ስብስባ ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም የኅብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ መካሄድ ይጀምራል።
ስብሰባው “ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ሥርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን ዓቀፍ፣ የሕይወት ዘመን ጥራትና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት“ በሚል የአፍሪካ ኅብረት ባዘጋጀው የ2024 መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ነው።
በስብሰባው ላይ የአፍሪካ ኅብረትና የኅብረቱ ተቋማት አመራሮች፣ የኅብረቱ አባል ሀገራት አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች እንደሚሳተፉበት ኢዜአ ከኅብረቱ ያገኘው መረጃ ጠቅሶ ዘግቧል።
ስብስባው የካቲት 5 እና 6 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚካሄደው 44ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ እንዲሁም የካቲት 9 እና 10 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚከናወነው 37ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ ረቂቅ አጀንዳዎች ላይ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም ኮሚቴው በአፍሪካ ኅብረት ስር የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትን የአፈጻጸም እንዲሁም ኅብረቱ እ.አ.አ በ2023 ያካሄዳቸውን ስብሰባዎች የተመለከቱ ሪፖርቶችን ያደምጣል።
ጥር 6 የሚጀምረው 47ኛው የአፍሪካ ኅብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ ስብሰባ እስከ ጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል። የአፍሪካ ኅብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ የኅብረቱን ቋሚ ተወካዮች እና የአባል ሀገራቱን አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ያቀፈ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!