ሦስት የአማራ ክልል ዩኒቨርስቲዎች ለተማሪዎች ጥሪ አደረጉ።

69

ባሕርዳር: ታኅሳሥ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚገኙት ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ እና ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲዎች የነባርና አዲስ ተማሪዎችን የመመዝገቢያ ጊዜ አስታውቀዋል።

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሰታወቀው የ1ኛ ዓመት ጀማሪ መርሐ ግብር 2ኛ ወሰነ ትምህርት እንዲሁም የ3ኛ ዓመትና ከዚያ በላይ ነባር መደበኛና የማታ ቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የመግቢያ ጊዜ ከጥር 15 እስከ ጥር 17/2016 ዓ.ም ድረስ መኾኑን አስታውቋል።

በ2016 ዓ.ም አዲስ የተመደቡ እና የማካካሻ መርሐ ግብር ተማሪዎች እንዲሁም በ2015 ዓ.ም የማካካሻ መርሐ ግብር ወስደው የማለፊያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ከጥር 21 እስከ ጥር 23/2016 ዓ.ም ድረስ እንዲመዘገቡ ዩኒቨርሲቲው ጥሪ አድርጓል።

በተመሳሳይ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት 2ኛ ወሰነ ትምህርትና ከዚያ በላይ ነባር መደበኛ የቅድመ-ምረቃ ተማሪዎች የመግቢያ ጊዜ ከጥር 16 እስከ 17/2016 ዓ.ም፣ የ2ኛ ዓመት 2ኛ ወሰነ ትምህርት ነባር መደበኛ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የመግቢያ ጊዜ ከጥር 23 እስከ 24/2016 ዓ.ም መኾኑን ይፋ አድርጓል።

የ1ኛ ዓመት 2ኛ ወሰነ ትምህርት ነባር መደበኛ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች እና የ2016 ዓ.ም አዲስ ገቢ የ1ኛ ዓመት ተማሪዎችም ከየካቲት7 እስከ 08/2016 ዓ.ም ድረስ እንዲመዘገቡ ዩኒቨርሲቲው ጥሪ አድርጓል።

ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲም የ2016 ዓ.ም ነባር መደበኛ ተማሪዎች የምዝገባ ጊዜ ጥር 2 እና ጥር 03/2016 ዓ.ም መኾኑን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ይፋ አድርጓል።

የትምህርት ሚኒስቴር በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ከጥር 01/2016 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 2 ሳምንታት የመማር ማስተማር ሥራ እንደሚጀምሩ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል ሲል ኢትዮጵያ ፕሬስ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ61 ሺህ በላይ ለሚኾኑ በራሳቸው አቅም ከፍለው መታከም የማይችሉ ነዋሪዎችን በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አካቶ ተጠቃሚ ለማድረግ ንቅናቄ መጀመሩን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳዳር ጤና መምሪያ አስታወቀ።
Next article47ኛው የአፍሪካ ኅብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ በቀጣዩ ሳምንት ይጀመራል።