
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “እንደ አቅሜ አዋጣለሁ፤ እንደ ህመሜ እታከማለሁ” በሚል መነሻ በከተማ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ በተዘጋጀው የኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የንቅናቄ መድረክ የባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ የከተማ እና ክፍለ ከተማ አመራሮች፣ የጤናው ዘርፍ አመራሮች እና ሙያተኞች እንዲኹም አጋር እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
በ2015 በጀት ዓመት የነበረውን በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አፈጻጸም እና የ2016 ዓ.ም እቅድ ቀርቦ ተገምግሟል የቀጣይ የትኩረት ነጥቦች ዙሪያ አቅጣጫ ተሰጥቶበታል።
የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በመድረኩ መክፈቻ በጤናው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ ለማስመዝግብ እና የሕዝብን ጤንነት በማረጋገጥ በኩል በመንግሥት የበጀት አቅም ብቻ የሚሸፈን ባለመኾኑ የተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ረጅ አካላትን አካቶ መሥራትን የሚጠይቅ ዋነኛ ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል።
በተለይም በራሳቸው ወጭ ከፍለው መታከም የማይችሉ ነዋሪዎችን በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን የህክምና ማዕቀፍ ውስጥ በማካተት ባለሃብቶችን፣ ነጋዴዎችን፣ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እና መሰል ማኅበረሰባዊ ኀላፊነታቸውን ለመወጣት ቅን የኾኑ አካላትን በማስተባበር በ2016 ዓ.ም 61ሺህ አዲስ እና ነባር ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ሲስተር ዓለም አሰፋ በንቅናቄ መድረኩ የአፈጻጸም ሪፖርት እና የቀጣይ እቅድ ሲያቀርቡ እንደገለጹት በከተማችን በዝቅተኛ የገቢ ምንጭ የሚተዳደሩ እና በራሳቸው ወጭ መታከም የማይችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ተጠቃሚ እንዲኾኑ ማድረግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
በዚህም በጥቂት ወጭ ብዙ ህክምና እንዲያገኙ፣ተጠቃሚዎች ስለ ህክምና ወጭ ሳያስቡ በወቅቱ ታክመው በቀላሉ መፈወስ እንዲችሉ ያደርጋል፣ በጋራ ወጭ የጋራ ህክምና እንዲገኝ ከማገዙም በላይ የበሽታ ሥርጭትን በእጅጉ ይቀንሳል፣ የመተጋገዝ ባሕል እና እሴት እንዲዳብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ትልቅ ተግባር እንደኾነም ገልጸዋል።
በያዝነው 2016 በጀት ዓመት እንደ ባሕር ዳር ከተማ ከ61 ሺህ 270 በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተጠቃሚ ለማድረግ የነባር አባላት እድሳት እና የአዳዲስ ተጨማሪ አባላት የማፍራት እንቅስቃሴ ውጤታማነት ከሚመለከታቸው የጤና ተቋማት ባለፈ አጋር እና ባለድርሻ አካላት ጭምር ልዩ ትኩረት ሰጥተው በመሥራት ጤናማ እና አምራች ማኅበረሰብ መገንባት ከሁሉም የሚጠበቅ እንደኾነ ሲስተር ዓለም አሰፋ ተናግረዋል።
በዚህ የንቅናቄ መድረክ በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አፈጻጸም ይስተዋሉ የነበሩ በተለይም የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት፣ ሒሳቦችን በወቅቱ አለማወራረድ፣ በጡረታ ከሥራ የተሰናበቱ ነዋሪዎች በዚሁ የህክምና ማዕቀፍ ያለመካተት የሚሉ እና መሰል ሃሳቦች በተሳታፊዎች ተነስተው በሚመለከታቸው የሥራ ኀላፊዎች ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል። የጤና ችግር የሁሉም ማኅበረሰብ የጋራ ጠንቅ በመኾኑ በጋራ መከላከል አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!