“ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር ለሚኖራት ሁለንተናዊ ትስስር የባሕር በር ስምምነቱ ትልቅ ትርጉም አለው” የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

38

ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት ኢትዮጵያን ከብሪክስና ከአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ተጠቃሚ የሚያደርግ መኾኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ።

በሥምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር ለመገንባት የሚያስችላትን ቦታ በሊዝ የምታገኝ ሲኾን ሶማሌላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ የልማት ኩባንያዎች ድርሻ እንደምታገኝ ተመላክቷል።

የመግባቢያ ሥምምነቱ ሂደት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ እንደሚገባም በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል።
ከዚሁ ስምምነት ጋር በተገናኘ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፤ የተደረሰው ስምምነት ኢትዮጵያን ከብሪክስና ከአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በላቀ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አራት ሀገራት በቅርቡ የተቀላቀሉበት ብሪክስ የዓለምን የገበያ ሥርዓት ከዩኒ-ፖላር ወደ ሁለትና ከዚያ በላይ አማራጭ ማስፋት የሚያስችል ስለመኾኑ አንስተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በብሪክስ እንቅስቃሴዋ ከአባል ሀገራቱ ጋር ለሚኖራት ሁለንተናዊ ትስስር በፍትሕዊ ዋጋ ወደ አባል ሀገራት በመላክ እና በማስመጣት ተጠቃሚ ለመኾን የባሕር በር ስምምነቱ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ነው ያሉት።

ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የሸቀጦች ታሪፍ ማቅረቧን አስታውሰው ከሶማሌላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት በዚህ ረገድ የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው በአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና አማካኝነት ምርቶችን ለአባል ሀገራቱ በማቅረብ ለጋራ ተጠቃሚነት ምቹ ኹኔታ የሚፈጥር መኾኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የባሕር በር ስምምነት ለአህጉራዊ ሁለንተናዊ ንግድና የልማት ትስስር እንዲሁም ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እና ደኅንነት የሚገባትን ሚና እንድትወጣ የሚያስችል መኾኑ ይታመናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት ባሳለፍነው ሳምንት መፈራረማቸው ይታወቃል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመሰረተ ልማት ግንባታዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው እንዲገነቡ እየሠራ መሆኑን ፌዴሬሽኑ ገለጸ።
Next articleከ61 ሺህ በላይ ለሚኾኑ በራሳቸው አቅም ከፍለው መታከም የማይችሉ ነዋሪዎችን በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አካቶ ተጠቃሚ ለማድረግ ንቅናቄ መጀመሩን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳዳር ጤና መምሪያ አስታወቀ።