የመሰረተ ልማት ግንባታዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው እንዲገነቡ እየሠራ መሆኑን ፌዴሬሽኑ ገለጸ።

43

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገሪቱ የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው እንዲገነቡ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች የሚመጥን የመሠረተ ልማት ግንባታ አለመኖር በርካቶችን ለከፍተኛ እንግልት እና የጤና ችግር እንደዳረጋቸው ይገለጻል። የመንገድ ላይ ምልክቶች አለመኖር፤ ሕንጻዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆን እና ሌሎች አገልግሎቶች አለመኖር ከሚጠቀሱ ችግሮች መካከል ይካተታሉ፡፡

ይህንንም ችግር ለመፍታት የሚከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ኢዜአ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽንን እና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንን አነጋግሯል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ በሀገሪቱ የሚገነቡ በርካታ መሰረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው እንደማይሰሩ ተናግረዋል፡፡

መሰረተ ልማቶች ከመገንባታቸው በፊት አካል ጉዳተኛውን ታሳቢ ያደረገ ንድፍ ከማዘጋጀት አንፃር የሚመለከታቸው ተቋማት በትኩረት ሊሠሩበት ይገባል ብለዋል።
ከህንጻ መሰረተ ልማት ምቹ አለመሆን ጋር ተያይዞ አካል ጉዳተኞች የሚያነሷቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ፌዴሬሽኑ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ጋር እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአዲስ አበባ የሚሠሩ የአዳዲስ መንገዶች ግንባታና የነባር መንገዶች እድሳት በሚከናወኑበት ወቅት ለአካል ጉዳተኛው ምቹ እንዲሆኑ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጋርም እየሠሩ መሆኑን አክለዋል።

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ ሰለሞን በበኩላቸው በመዲናዋ በርካታ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት የመንገድ መሰረተ ልማቶች አካል ጉዳተኛውን የማኅበረሰብ ክፍል ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲገነቡ የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኩር ጋዜጣ ታኅሳስ 29/2016 ዓ.ም ዕትም
Next article“ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር ለሚኖራት ሁለንተናዊ ትስስር የባሕር በር ስምምነቱ ትልቅ ትርጉም አለው” የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር