
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በቅዱስ መጽሐፍ ያለው የተገለጠባት፤ በሰማይ ያለው በምድር የታየባት፤ በልቡና ያለው በእውን የተቀረጸባት፤ ተስፋ የሚደረገው ተቀርጾ የጸናበት፤ ቃል ኪዳን የተሰጠባት፤ የጸናባት፤ የዓለም ጥበብ ሁሉ የተናቀባት፤ ለዓለሙ ሁሉ አዲስ ጥበብ የታየባት፤ ተፈጽሞ የተጀመረባት፤ ንጉሡ የረቀቀውን የፈጸሙባት የተዋበች፣ የተመረጠች ምድር፡፡
ሰማይን የመሠለች፤ በሰማዊት እና በምድራዊት ኢየሩሳሌም አምሳል የታነጸች፤ ዳግማዊት ኢየሩሳሌም የተሰኘች፤ ለዓለሙ ዓይን ሁሉ ድንቅ የኾነች፤ ታሪኳ ይሰማ ዘንድ ጀሮን ያስዘነበለች፤ ታሪኳን ይናገሩላት ዘንድ አንደበትን ያሰላች ቅድስት ሥፍራ፡፡
በዚያች ምድር ድንጋይ አጊጦባታል፤ ዓለት ተውቦባታል፤ እንደ አሽከር ታዝዞበታል፤ በጸርሐዓርያም የታየ ምስጢር በምድር ተገልጦበታል፤ ዓለት መሰሶም፣ ጣሪያም፣ መሠረትም፣ ግድግዳም ሁሉንም ሆኖባታል፤ ዘወትር ድንቅ፣ እያደር ረቂቅ የኾነ የምስጢር ማሕተም ታትሞባታል፡፡ በዚያች ምድር ምድራዊ ንግሥና ከሰማያዊ ቅድስና ጋር ተስማምተውባታል፤ ሰውና መልእክት ተባብረውበታል፡፡
በቤተ መንግሥት የነገሡት፣ ባማረ ዙፋን ላይ የተቀመጡት፣ በትረ መንግሥት የጨበጡት፣ በእንቁ የተዋበ ዘውድ የደፉት፣ በተዋበ ሠረገላ ተቀምጠው የሚመላለሱት ንጉሥ በቤተ ክህነትም ቅዱስ ናቸው፡፡ ንግሥናቸው ቅድስናቸውን ያልተጋፋባቸው፤ ምድራዊ ሃሳብ ሰማያዊ ሃሳባቸውን ያልበረዘባቸው፤ የቤተ መንግሥቱ አጀብ የቤተ ክህነቱን ምሥጋና ያላቋረጠባቸው፤ የቤተ መንግሥቱ ተድላና ደስታ ከጾምና ከምሕላ ያላሰናከላቸው፤ በቀኝ እና በግራቸው፣ በፊትና በኋላቸው የሚከባቸው መልአክትን ያላስረሷቸው፤ በአጠገባቸው የማይለዩዋቸው መኳንንት ቅዱሳን አበውን ያላስዘነጓቸው ለቅድስናም ለንግሥናም ምሳሌ የኾኑ ናቸው፡፡ ሳያቋረጡ ምሥጋና ያቀርባሉ፤ ከሰው መርጦ የቀባቸውን፣ በሕዝብ ዘንድ ይፈርዱ ዘንድ ስልጣን የሰጣቸውን አምላካቸውን ያመሠግናሉ ቅዱስ ወ ንጉሥ ላሊበላ፡፡
ንጉሥ ወቅዱስ ላሊበላ በቤተ ክህነት ገድል ከተጻፈላቸው፣ ታቦት ከተቀረጸላቸው፣ በቤተ መንግሥትም የከበረ ታሪክ ከተጻፈላቸው፣ ከፍ ያለ ክብር ከሚሰጣቸው ኢትዮጵያውያን ነገሥታት እና ቅዱሳን መካከል አንደኛው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከምታጌጥባቸው፣ በዓለሙ ፊትም ተከብራ ከምትታይባቸው፣ ከዓለሙም ከምትለይባቸው ድንቅ አሻራዎች መካከል እሳቸው የሠሯቸው አብያተ ክርስቲያናት ከፊት ይጠቀሳሉ፡፡
ተክለጻዲቅ መኩሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ ኑብያ አክሱም ዛጉዬ እስከ አፄ ይኩኑ አምላክ ዘመነ መንግሥት በተሰኘው መጽሐፋቸው ሙሴ ኮንቲ ሮሲኒን ጠቅሰው ስለ ላሊበላ ሲጽፉ “ በሀገሩ ንጉሡ በጣም ኀያል ገናና ነው፡፡ የግዛቱን ዙሪያ ከበዓል ቀን በቀር ዙሪያውን በእግር ለማዳረስ የአንድ ዓመት ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ዘውድ ደፍቶ የነገሠው በቅዱስ ገብርኤል እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በመንበረ ዳዊት ተቀምጦ ለዜጎቹ ፍርድ ይሰጣል” ብለዋል፡፡ እኒህ ንጉሥ ግዛታቸው የሰፋ ኀያል እና ጠቢብ ናቸው፡፡
ንጉሥ ወ ቅዱስ ላሊበላ ያሠሯቸው አብያተ ክርስቲያናት በሰርክ ቢነገርላቸውም፣ በሠርክ ስለ ውበታቸው እና ስለ ሚስጢራዊነታቸው ቢመሰከርላቸውም ልደት በደረሰ ጊዜ ደግሞ ከወትሮው በልጠው ይታያሉ፤ ይታወሳሉ፡፡ ከአራቱም ንፍቅ የመጣን ሕዝብ ያሰባስባሉ፡፡ እልፍ አዕላፍ በኾነ ሕዝብ ይከበባሉ፡፡
በበዓለ ልደት በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ቢፈጸምም፣ የጌታ ልደት ቢታሰብም በተቀደሰችው ምድር በላሊበላ ግን ከሁሉም ይልቃል፡፡ ስለ ምን ይህ ኾነ?
የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም አሥተዳደሪ አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ የጌታ ልደት የነጻነት አዋጅ የታወጀበት፤ ከባርነት የወጣንበት ነው ይላሉ፡፡ የሰው ልጅ ነጻነቱ ይሰጠው ዘንደ በምድር ላይ እርቅ ተጀመረ እንደተባለ የጌታ ልደት ነጻነት የተጀመረበት ነው፡፡ ቅዱስ ላሊበላ በተቀበሉት ቃል ኪዳን እና ባነጿቸው ውብ አብያተ ክርስቲያናት አማካኝነት የልደት በዓል በቅዱስ ላሊበላ ልዩ ይኾናል ነው የሚሉት፡፡
“ በዚህ ቦታ በዓለ ልድትክን ከበዓለ ልደቴ ጋር አንድ አድርጎ የሚያከብር፤ በዚህ ቀን መጥቶ የተሳለመ ቤተልሔምን እንዳዬ እና እንደተሳለመ እቆጥርለታለሁ” የሚል ቃል ኪዳን ተሰጥቷቸዋል፤ ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም ያለ ጌታ ከሰጠው ቃል ኪዳን የሚካፈሉ ምዕመናን ወደ ላሊበላ ያቀናሉ፡፡ በተቀደሰች ስፍራም በረከትን ይቀበላሉ ይላሉ አባ ሕርያቆስ፡፡
የሰማያዊያን መልአክት እና ብስራቱን የተቀበሉ ምድራዊን ምሳሌ የኾነችው ቤተ ማርያም በዚያች ስፍራ ታንጻለች፡፡ ቅዱስ ላሊበላ በዓለ ጽንሰታቸውም፣ በዓለ ልደታቸውም ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ጋር ተመሳሳይ ነው ይላሉ፡፡
ዲያቆን ፈንታ ታደሰ የዐራቱ ቅዱሳን ነገሥታት እና የአካባቢው ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው “ ቅዱስ ላሊበላ የተጸነሰበት እና የተወለደበት ቀን ሲነጻጸር ከፈጣሪው ጋር አንድ ቀን ነው፡፡ ጽንሰታቸው እና ልደታቸው የሚለያየው በዓመተ ምሕረት ነው” ብለው ጽፈዋል፡፡
ቅዱስ ላሊበላ የተዋቡትን አብያተ ክርስቲያናት አንጸው ካጠናቀቁ፣ ቃል ኪዳንም ከተቀበሉባቸው በኋላ ክርስቲያኖች በረከትን ለማግኘት ወደ ዚያች የተቀደሰች ስፍራ ይጎርፋሉ፡፡ ድንቅ ነገር ላይ በምድር ላይ ተሠርታለች እና የቀደሙ አባቶች ለበረከት ሲሉ በባዶ እግራቸው ይተማሉ፤ በረከት ወደ አለባት ስፍራ መትመምም የተለመደች ናት ነው የሚሉት፡፡ ደጋጎቹ ሃብትና ንብረት እያላቸው በረከትን አብዝተው ይቀበሉ ዘንድ በቅሎዎቻቸውን ትተው፣ ፈረሶቻቸውንም ረስተው በባዶ እግራቸው ወደ ቅድስቷ ስፍራ ይጓዙ ነበር፡፡ ዛሬም ብዙዎች በሰማይ መብረሩን፣ በምድር መሽከርከሩን ትተው ለበረከት በባዶ እራቸው ይጓዛሉ፡፡ ስለ ምን ቢሉ ቃል ኪዳን በጸናባት ቅድስት ሥፍራ የአምላክ በረከት አለችና፡፡
ጌታ በተወለደ ጊዜ ቅዱሳን መልአክት ጌታ ተወልዷል እያሉ አብስረዋል፤ በሰማይና በምድር ምሥጋና ይሁን እያሉ አመሥግነዋል፡፡ በቤተ ልሔም የሰማይ መልአክት እንዳመሰገኑ ሁሉ በቅዱስ ላሊበላም ሊቃውንቱ ቤዛ ኩሉ እያሉ ምሥጋና ያቀርባሉ፡፡ ይሄም ድንቅ ነገር ነው፡፡ ሰው እና መልአክት በአንድ ላይ ኾነው ያመሠገኑበትን ያስባሉ፣ ያስታውሳሉ፡፡ ሊቃውንቱም ለአምላካቸው ምሥጋና ያቀርባሉ፡፡ ይህም ሥርዓት ቅዱስ ላሊበላን የበለጠ ልዩ ያደርገዋል፡፡
አባ ሕርያቆስ እንደሚሉት አምላክ በቅዱሱ አድሮ አብያተ ክርስቲያናትን እንዳሠራቸው ሁሉ በአባቶቻችን አድሮ ሥርዓት ሠርቶልናልና ሥርዓቱ የዓለምን ቀልብ ይስባል፡፡ የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ሰማያዊ የኾኑ ምስጢራዊ ጓዳዎችን የሚያሳዩ ናቸው፤ ክርስቲያኖች የተጻፈችውን ተስፋ እንዲያዩዋት ቅዱሱ ሠርተውላቸዋልና፡፡ የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት ነው እንደተባለ ይላሉ አባ ሕርያቆስ የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት የቀደሙት አባቶች ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ጥልቅ ግንኙነት፣ እግዚአብሔርን መፍራት ለእንዲህ አይነት ጥበብ እንደሚያበቃ የሚገለጥበት ነው ይላሉ፡፡
የቅዱሳኑ ድንቅ ጥበባቸው እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ የትናንት አባቶች የነበራቸውን ጥበብ ማሳያ ነው፤ ከሃይማኖት ባሻገርም የትናትን ስልጣኔ መግለጫ ነው፣ ለነገም ጥሩ መነሻ፣ የአባቶችን ጥበብ መጠቀም የት ሊያደርስ እንደሚችል ማመላከቻ፣ እግዚአብሔር የሰጠን መልካችን እና ውበታችን ነውም ይሉታል፡፡
አባቶች ጥበብን ተጠቅመውበት አልፈዋል፤ የአባቶችን ጥበብም እንጠቀም ዘንድ ግድ ይላል፤ ወደ ቅዱስ ላሊበላ የሚመጡ ወገኖች ታሪካቸውን ፣ ማንነታቸውን እና ሃይማኖታቸውን ገዝፎ ያዩበታል ነው ያሉት፡፡ ለዚህ ትውልድ ከአባቶች የሚበልጡበት ነገር እንደሌለ ያስብ፣ የቀደሙትን የአባቶችን ፈለግ እና ሥርዓት ይከተል፤ አባቶች የደረሱበትን ጸጋ ይረዳ፣ ምንም ሳይኖረው እንዳለው አይቁጠር ይላሉ አባ ሕርያቆስ፡፡
በገድለ ቅዱስ ላሊበላ “ የአምላክ ሰው ቅዱስ ላሊበላ ንጉሥ ሲኾን በሎሌ የተመሰለ ነው፡፡ የቤተሰብ ጌታ ሲኾንም በቤተሰብ የተመሰለ ነው፡፡ የመኳንንት ጌታ ሲኾን በተገዥ የተመሰለ ነው፡፡ የጾምን ፍሬ ከትዕግስት ፍሬ ጋር የትሩፋቱን ፍሬ አሳየ፤ የትሕትናንም ፍሬ ከመዋረድ ፍሬ ጋር፤ የጸሎትንም ፍሬ ከቅንነት ፍሬ ጋር፤ የስግደትን ፍሬ ያለ ሰይፍና ያለ መረገጫ ከሰውነት የምትፈስ የሰማዕት ደም የምትመስል ላበትን ከማንጠፍጠፍ ጋር የንጽሕናንም ፍሬ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከመገስገስ ፍሬ ጋር፡፡ እንግዳ የመቀበል ፍሬንም ከምጽዋት ጋር፤ የፍቅርንም ፍሬ ከደግነት ፍሬ ጋር፤ የማክበር ፍሬንም ፈጽሞ ከማመስገን ፍሬ ጋር ፤ ከቀደሙ ቅዱሳን የበጎ ምግባራቸውን ፍሬ ሰብስቦ ገንዘብ አደረገ፡፡ ይህችውም የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ናት” ተብሎ ተጽፏል፡፡
እሳቸው የተወደደችውን ሁሉ ሀብታቸው ያደረጉ ናቸው፡፡ በቤተ መንግሥቱም በቤተ ክህነቱም የተመረጡት፤ የተመሰገኑት፣ ቅዱስም ንጉሥም የኾኑት አበው ስማቸው በታሪክ ከፍ ብሎ ይኖራል፡፡ በትውልድም ልብ እየተጻፈ ይሸጋገራል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!