“ፍቅር፣ ደስታ እና ሰላምን አጥብቃችሁ ያዙ” ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ.ር)

47

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጻድቁ የቅዱስ ላሊበላ የልደት በዓል በዳግማዊቷ ኢየሩሳሌም ላሊበላ እየተከበረ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና በሀገረ አሜሪካ የኒዩርክ እና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ.ር)፣ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ኤርምያስን ጨምሮ በርካታ ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተዋል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና በሀገረ አሜሪካ የኒዩርክ እና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ.ር) ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም ወዕጨጌ ዘ መንበረ ተክለሃይማኖት እንዲኹም ከሌሎች አባቶች የተላኩትን ቡራኬም ለሕዝበ ክርስቲያኑ አድርሰዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ.ር) በንግግራቸው እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ፤ ለጻድቁ እና ለቅዱሱ ለላሊበላ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ.ር) ሕዝበ ክርስቲያኑ ፍቅርን፣ ሰላምን እና ደስታን አጥብቆ እንዲይዝ መክረዋል፡፡

በታላቁ መጽሐፍ በዮሐንስ ወንጌል ላይ “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጠን ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶታል” ተብሎ ተጽፏል ነው ያሉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ.ር)፡፡ እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ አምላክ ሳለ ለሰው ልጆች ከነበረው ፍቅር የተነሳ ሰው ኾኖ ከድንግል ማርያም መወለዱን ተናግረዋል፡፡ እግዚያብሔር በምድር ላይ ፍቅርን፣ ደስታን እና ሰላምን ያለገደብ መሥጠቱንም ተናግረዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ.ር) የሰው ልጅ በፍቅር እንዲኖር አጥብቀው ጠይቀዋል፤ ፍቅር ደግሞ ክርስቶስ በስጋ መገለጡ ነው ብለዋል፡፡ “ዓለም በሮማውያን ቅኝ ግዛት በወደቀበት ጊዜ እግዚአብሔር አንድ ታምር አደረገ የሚሉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ(ዶ.ር) እናቱ ድንግል ማርያም ከናዝሬት ወደ ቤተልሔም ሄደች፤ በከብቶች በረትም ተጠጋች፤ በዚያም ሳለች አንድያ ልጇን ወለደች፤ ዓለም ለቅዱሳን ቦታ አልነበራትምና ኢየሱስ ክርስቶስም በበረት ተወለደ” ብለዋል፡፡

ዘመኑ ጨለማ ቢኾንም ተራራው በብርሃን ተጥለቀለቀም ሲሉ ያብራራሉ፡፡ መላኩም ወደ እረኞች ሄዶ “አይዟችሁ አትፍሩ” ዛሬ በዳዊት ከተማ አዳኝ ክርስቶስ የዓለሙ ሁሉ ንጉስ ተወልዷል ብሏቸዋል ነው ያሉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ.ር)፡፡ ለዚህም ፍቅር፣ ሰላም እና ደስታ ተሰበከ ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ እረኞች እና መላዕክት በአንድ ላይ ዘምረዋልም ብለዋል፡፡ ተጣልተው የነበሩት ሰው እና እግዚአብሔር፤ ሰው እና መላዕክት እርቅ አውርደዋል ነው ያሉት፡፡

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ.ር) ክርስቲያኖች ተስፋ እንዳይቆርጡ በርካታ ቅዱሳን ለኢትዮጵያ ሰዎች ተሰጥተዋቸዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ቅዱስ ያሬድ እና ቅዱስ ላሊበላ ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው ነው ያሉት፡፡

ሰዎች ሰላምን፣ ደስታን እና ፍቅርን መፈለግ አለባቸው ያሉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ.ር) እግዚያብሔር በበረት የተወለደው ለሰው ልጆች ፍቅር እና ሰላምን ለመስጠት ነው ብለዋል፡፡

የዛሬ 800 ዓመት የቤተ ክርስቲያን ከተማ የመሠረቱልንን አባቶቻችንን ልናከብር እና ልናመሠግናቸው ይገባል ያሉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ.ር) በዚህ ቀን በዳግማዊቷ ኢየሩሳሌም በላሊበላ ተገኝተን የኢየሱስ ክርስቶስ እና የጻድቁን የቅዱስ ላሊበላን በዓለ ልደት በጋራ እንድናከብር አስችለውናል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ.ር) ፍቅርን ተለማመዱት ፍቅር አፍቃሪ ልብን፣ አፍቃሪ ሰዎችን ትሻለችና ነው ያሉት በመልዕክታቸው፡፡ ሰው ሦስት ጊዜ ዝም ይላል ሲያዝን፣ ሲደሰት እና ሲደነቅ ያሉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ.ር) “ቅዱሳን በሠሩት በቤተክርስቲያን ከተማ ከመደነቄ ብዛት ዝም አልኩ” ብለዋል፡፡

በትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዓባይ ቴሌቪዥን፣ የኅብረተሰቡን መልካም ባህል እና ዕሴት የሚጥስ ሃሳብ ያለበት ፕሮግራም አስተላልፏል በሚል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን የብዙኃን መገናኛ ባለስልጣን ገለጸ።
Next article“ሰማይን የመሠለች፣ ዳግማዊት ኢየሩሳሌም የተሰኘች”