
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይ ቴሌቪዥን፣ የኅብረተሰቡን መልካም ባህል እና ዕሴት የሚጥሱ ሐሳብ ያለበት ፕሮግራም አስተላልፏል በሚል በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን የኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ባለስልጣን ገልጿል።
ባለሥልጣኑ ለቴሌቪዥን ጣቢያው በጻፈው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ፣ “ዓባይ ቴሌቪዥን እሑድ ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ‘ዋሸሁ እንዴ?’ በተሰኘ ፕሮግራሙ ላይ የሴቶችን ስብዕና፣ መብት እና ክብር የሚያጎድፉ እንዲሁም የኅብረተሰቡን መልካም ባህል እና ዕሴት የሚጥሱ በተለይም በሴት ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀልን የሚያበረታቱ እና ታዳጊዎችን ላልተገባ ድርጊት የሚዳርጉ ሐሳብ እና አስተያየቶች በፕሮግራሙ ላይ መተላለፉን ባለሥልጣኑ ያደረገው የሚዲያ ይዘት ክትትል ግኝት የሚያመለክት ሲሆን ከኅብረተሰቡም ጥቆማዎች ቀርበዋል” ብሏል።
በዕለቱ የተሠራጨው ፕሮግራም የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238/2013 አንቀጽ 68/2 ለ/ሐ/መ/ እና ሠ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የጣሰ ሆኖ መገኘቱን ነው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የጠቆመው።
አክሎም፣ “ዓባይ ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ የኅብረተሰቡን መልካም ዕሴት፣ ሰላም እና ደኅንነት የሚያናጉ ፕሮግራሞች እና ዘገባዎችን በጣቢያው ሲያሠራጭ ከባለሥልጣኑ በኩል በተለያዩ መንገዶች ግብረ-መልሶችን በመስጠት እንዲሁም ከጣቢያው ኃላፊዎች ጋር ውይይቶችን በማካሄድ ጭምር መሻሻሎች እንዲደረጉ ጥረት ቢደረግም ጣቢያው ይህን መሰል ድርጊቶችን ለማረም አልቻለም” ሲል ገልጿል።
በመሆኑም ጣቢያው በቀጣይ መሰል ሕግን የሚጥሱ፣ ኃላፊነት የጎደላቸው፣ የሰውን ልጅ ስብዕና እና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ፕሮግራሞችን ከማሠራጨት እንዲቆጠብ ይህ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው አሳስቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!