
ባሕርዳር: ታኅሳሥ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቤዛኩሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓት በላሊበላ በድምቀት እየተከበረ ነው። ይህንን ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት ዜጎች በቦታው ተገኝተው ተከታትለውታል።
የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ የበላይ ጠባቂ ብጹዕ አቡነ ፊሊጶስ ከውጭ ለመጡ እንግዶች በእንግሊዝኛ ቋንቋ መልእክት አስተላልፈዋል።
ብጹዕ አቡነ ፊሊጶስ በመልእክታቸው “ላሊበላ ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ናት” ብለዋል። “በዓሉን ለማክበር ከውጭ ሀገር እና ከሀገር ውስጥ ተጉዛችሁ በቅዱስ ላሊበላ የተገኛችሁ ሁሉ መንፈሳዊ መባረክን ታገኛላችሁ” ሲሉም ገልጸዋል።
ለኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በኢየሩሳሌሟ ቤተልሄም ከተማ ፍጥረታት ሁሉ በአንድነት እንደዘመሩ ሁሉ እኛም በላሊበላ ተገኝተን ልደቱን በጋራ እየዘመርን እያከበርን ነው ብለዋል።
በቤዛ ኩሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ቀሳውስት እንደ መላዕክት ከላይ ኾነው በዝማሜ፣ ምዕመናን ከታች ኾነው በእልልታ ሲዘምሩ የሰማይ መላዕክታንን እና የምድር ፍጥረታትን ትሥሥር የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ብጹዕ አቡነ ፊሊጶስ እኛ የምንዘምረው ለኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነው፤ ልደቱም በምድር ላይ ያለውን ክፉ ነገር ሁሉ አስወግዶ ምድርን በሰላም የሞላ ስለነበር ነው ሲሉ ተናግረዋል። ለዚህም ነው የልደቱን በዓል በድምቀት የምናከብረው ብለዋል።
ብጹዕ አቡነ ፊሊጶስ “ኢየሱስ ክርስቶስ አማራጭ የሌለውን ምርጫ አሳይቶናል፤ እሱም ሰላም ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወደ ምድር ሲወርድ በሰው ልጆች ዘንድ የነበረውን መጠላላት እና ክፉ ነገር ሁሉ አስወግዶ ሰላምን፣ ፍቅርን እንዲሁም አንድነት ለማምጣት ነው ብለዋል።
እኛም ኢየሱስ ክርስቶስ ካሳየን ነገር መማር አለብን ሲሉ ተናግረዋል። ከሰማይ ወደ ምድር መውረዱ ለሰላም እና ለፍቅር መኾኑን በመገንዘብ እርስ በእርስ ከመጠላላት እንውጣ፤ በመካከላችን ፍቅርን እና አብሮ መኖርን እናንግሥ ነው ያሉት በመልእክታቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!