“የበዓሉን አከባበር ሃይማኖታዊ ተምሳሌት ወስደን ለሰላም መሥራት አለብን” ዲያቆን ተስፋው ባታብል

18

ባሕርዳር: ታኅሳሥ 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ2016 ዓ.ም የልደት በዓል በደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም እየተከበረ ነው። የቤዛ ኩሉ ሥነ ሥርዓት ተከውኗል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል “የበዓሉን አከባበር ሃይማኖታዊ ተምሳሌት ወስደን ለሰላም መሥራት አለብን” ብለዋል።

ኮሚሽነሩ ቅዱስ ላሊበላ እና በዙሪያው የሚገኙ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት የኢትዮጵያውያን ታላቅነት ማሳያዎች መኾናቸውንም ጠቅሰዋል። ”የኢየሱስ ክርስትስ ልደት ሃይማኖታዊ በዓል የተጣሉ የታረቁበት፣ ፍቅር የተሰበከበት፣ አንድነት የታወጀበት፣ የፍቅር እና የነጻነት በዓል ነው” ያሉት ዲያቆን ተስፋው በዓሉን ከመላው ዓለም እና ከሁሉም ማዕዘናት የተሰበሰቡ ኢትዮጵያውያን በዘር፣ ቋንቋ፣ ሐይማኖት እና ብሔር ሳይገድበን በድምቀት በማክበራችን ኩራት ሊሰማን ይገባል ብለዋል።

”ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በአንድ ልብ ለጋራ ዓላማ የሚቆሙ፤ ለጋራ ሁለንተናዊ እድገት የሚታትሩ፤ በአንድ መንፈስ ሀገራቸውን የሚወዱ እና በሕብረት ደምቀው እንደ ችቦ የሚያበሩ እውነተኛ ኢትዮጵያውያን ናቸው” ብለዋል። በበዓሉ የታየው ትብብር እና ሕብረትም የዚሁ አንደነት ነጸብራቅ መኾኑን ጠቅሰዋል።

ዲያቆን ተስፋው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል የሀገሪቱን ሰፊ እና እምቅ የቱሪዝም ሃብት ለማሳየት የሚቻልበት መኾኑን እና በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም የቱሪዝም ዘርፉ ማመንጨት የሚችለውን እንዲያመነጭ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሰላም የሁሉ ነገር ዋስትና በመኾኑ ከምንተነፍሰው አየር ያልተናነሰ ትልቅ ዋጋ አለው ያሉት ዲያቆን ተስፋው ”ከፍክክር ይልቅ ትብብርን፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፣ በመንገዳችን ሁሉ ልናስቀድም ይገባል” ብለዋል።

ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ አገልግሎት ለሰጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የጸጥታ ኃይሎች፣ ለላሊበላ እና አካባቢው ነዋሪዎችም ምስጋና አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleማኅበረ ቅዱሳን በደቡብ ወሎ ዞን ጃሪ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የእርድ እንስሳትን ድጋፍ አደረገ፡፡
Next article“ኢየሱስ ክርስቶስ አማራጭ የሌለውን ምርጫ አሳይቶናል፤ እሱም ሰላም ነው” ብጹዕ አቡነ ፊሊጶስ