
ደሴ: ታኅሳሥ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን በደቡብ ወሎ ዞን ጃሪ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የእርድ እንስሳት ድጋፍ አድርጓል።
ማኅበሩ የተለያዩ በጎ አድራጊ ማኅበራትን በማስተባበር በሁለት መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ነው ከ360 ሺህ ብር በላይ ወጭ በማድረግ የእርድ እንስሳት ድጋፍ ያደረገው፡፡
ከተለያዩ አካበቢዎች ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ አካባቢ በሚገኛው ጃሪ የመጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች በተለያየ ችግር ውስጥ ኾነው ዓመታን ማሳለፋቸውን ይናገራሉ፡፡ በመንግሥትም እና በበጎ አድራጊ ማኀበራት ድጋፍ እየተደረገላቸው መቆየታቸውን የገለጹት ተፈናቃዮቹ በቅርቡ ወደየቀያቸው ትመለሳለችሁ ስለተባለ ያለቸውን ሁሉ እንደጨረሱ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም በችግር ውስጥ ኾናቸውን ነው የሚጠቅሱት፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በበዓል ወቅት ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡ የሰላም እጦት ከመኖሪያ ቀያችን አፈናቅሎናል፤ ሰላም የሁለም ነገር መሰረት በመኾኑ በመላ ሀገሪቱ ሰላ ሰፍኖ ማየትን እንሻለን ብለዋል፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን የደሴ ማዕከል ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን ሞላ ንጉስ የተፈናቀሉ እና በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናረዋል፡፡ የተለያዩ በጎ አድራጊ ማኅበራትን በማስተባበር በሁለት መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ከ360 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ የእርድ እንስሳትን ድጋፍ እንዳደረጉም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ዲያቆን ሞላ ሰብዓዊነት የሚሰማው ሁሉ እነዚህን ወገኖች ሊመለከታቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ:- ደጀን አምባቸው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!