የነጻነት ምልክት የልደት ጌጥ የገና ጨዋታ!

46

ባሕርዳር: ታኅሳሥ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የገና ጨዋታ ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደተጀመረ በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል እሴቶች ባለሙያ አቶ ደርበው ጥላሁን ይገልጻሉ፡፡

እንደባለሙያው ገለጻ ጨዋታው አዝመራ ከተሰበሰበበት ታኅሣሥ ወር ጀምሮ እስከ ጥር ይከናወናል። አልፎ አልፎም ክረምቱ መግቢያ ድረስ ጨዋታው የሚቀጥልበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ በተለይም በጥምቀት በዓል ወጣቶች ተሰባስበው ታቦታቱን አጅበው ወደ ቤተመቅደሳቸው ካስገቡ በኋላ ጎራ ለይተው ይጫወታሉ፤ ቦታው ደግሞ ለጥ ባለ ሜዳ ላይ ኾኖ የጠነከረችው ፀሐይ ቀዝቀዝ ስትል ከሰዓት በኋላ ያከናውናሉ፡፡

የገና ጨዋታ አሳታፊ በመኾኑ ብዙ ተመልካች የለውም፤ ተጫዋች እንጅ፡፡ ጨዋታው ሩሯ ለዓይን መታየት እስከቻለችበት ጊዜ ድረስ እንደሚከናወን አቶ ደርበው ጠቁመዋል፡፡

ቡድኖች እንዴት ይቋቋማሉ?

ባሕላዊው ጨዋታ የሚካሄደው በሁለት ቡድኖች መካከል ነው፡፡ ቡድኖቹ የሚዋቀሩት ሁለት በሽምግልና፣ በነገር አዋቂነት፣ በሐብት መጠናቸው ስመ ጥር የኾኑ አባቶች ይመረጣሉ፡፡ እነዚህ ለምድር የከበዱ አባቶች ገና ለመጫወት የተሰበሰበውን ሕዝብ በሚስጢር ለምሳሌ፦ ” አንዱን አንበሳ ሌላውን ነብር ” ዓይነት ኾኖ እንዲቧደን ይጠይቃሉ፡፡ አባቶቹ ሁሉም ሰው መቧደኑን ካረጋገጡ በኋላ ” አንበሳ የኾንህ ወዲህ፤ ነብር የኾንህ ወዲያ ” በማለት ቡድን ያቋቁማሉ ሲሉ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

በቡድን አባቶች ምርጫ የሚጫወቱት ገና አንዱ በጨዋታው ተጎድቶ ቢወጣ ወይም እንግዳ ሰው ለመግባት ቢፈልግ ለጎበዝ አለቃው ወይም ለአጫዋቾቹ ተናግሮ ሲፈቀድለት ብቻ የሚገባ ይኾናል፡፡

ዘግይተው የመጡት የገና ተጫዋቾች ደግሞ የተለየ ስም በመያዝ ትከሻ ለትከሻ በመያያዝ ከሁለቱ የቡድን አባቶች ፊት እየቀረቡ ወደ ቡድናቸው እንዲቀላቀሉ ይደርጋሉ፡፡

በአንዳንድ አካባቢ የገና ጨዋታ በሚከወንበት ጊዜ አንድ የጎበዝ አለቃ አስጀማሪ እና ጨዋታውን የሚመሩ አራት የድንበር ጠባቂዎችን ይሰይማሉ ብለዋል፡፡
ጨዋታው በመንደር ወይም በቀበሌ ሊኾን ይችላል፡፡ባገቡና ባላገቡ መካከልም ሊካሄድ ይችላል፡፡

የገና መጫዎቻው ከጫፉ ቆልመም (ቀለስ) ያለ እንጨት ነው፡፡ የመጫወቻ ሩሯም /ጥንጓም/ ከቆዳ ወይም ከዛፍ ስር ተጠርባ የምትወጣ ድቡልቡል ኾና የምትዘጋጅ ናት፡፡
ጨዋታው ግብ ግብ ፣ ግፊያና ሽምጥ እሽቅድምድም ስላለው አካላዊ ጥንካሬ እና ቅልጥፍና ያላቸው፣ ተጋፍተው ማለፍ የሚችሉ ሰዎች ይጫወቱታል፡፡

ሕጻናት ፣ አረጋዊያን እና አቅመ ደካማዎች እንዲጫወቱ አይመከርም ብለዋል ባለሙያው ፡፡

ጨዋታው የተለያየ አይነትም ነው። ከጨዋታው ውስጥ “ቁርቁዝ” እንዱ የጨዋታ ዓይነት ነው፡፡ ይህ የጨዋታ ዓይነት ሕግን በመከተል “በሚናህ” (በቦታህ) በማለት ጥንጓን በኀይል ሳይመቱ በማንከባለል ብቻ የሚጫወቱት የጨዋታ ዓይነት ነው፡፡

“ሙጭ”ሌላው የጨዋታ ዓይነት ነው፡፡ ይህ ሁለቱ ቡድኖች በመጥረግ ብቻ እንጫወት ብለው በመስማማት የሰውንም አግር ኾነ ጥንጓን በመጥረግ የሚጫወቱት ነው፡፡
“ቀልቦ መለጋት” የተሰኘው ጨዋታ ከባዱ የጨዋታ ዓይነት ነው፡፡ ሩሯን አፍሶ የመለጋት ጨዋታ ነው ብለዋል አቶ ደርበው፡፡

የገና መለያ

የተጫዋቾች አለባበስ ጉልበት ላይ የሚቀር ሱሪ፣ እጀ ጠባብ፣ ባተ ተሁለት እና ከወገብ ላይ የሚጠመጠም “ድጌ” ለብሰው ይጫወታሉ ብለዋል ባለሙያው፡፡

የገና ጨዋታ የሁሉም ጨዋታ መኾኑን ለመግለጽ “በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ፤ በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” እየተባለ ይከናዎናል። በተጫዋቹ ላይ አደጋ ቢደርስ ቂም መያዝና ለበቀል መነሳሳት አይታሰብም፤ አይሞከርምም።

ለመኾኑ “በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ፤ በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” አንድምታው ምን ይኾን?

በተፎካካሪ ቡድኖች መካከል ከሐሳብ አንስቶ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ትችት እና ነቀፌታ ይዘንባል። አንዳንዴም እስከ ስድብ ይደርሳል። መነቃቀፉ ጨዋታው የነጻነት መገለጫ መኾኑን የሚያመላክት ነው። ማንም ማንንም ከመንቀፍ የሚያግደው ወይም የሚያስፈራው ነገር አይኖርም።

በዚህ ወቅት ስጋት የኾነባቸውን ተወዳዳሪ ለማኮሰስ፣ የሠራውንም፣ ያልሠራውንም እየዘረዘሩ ድክመቱን እንደ ተራራ አግዝፈው ሊያሳዩ ይጥራሉ። ለምሳሌ፦

‹‹ወንድ ነው ብዬ … ብሰጠው ጋሻ፣
ለናቱ ሰጣት ላመድ ማፈሻ፡፡
ወንድ ነው ብዬ ብሰጠው ጦር፣
ላባቱ ሰጠው ለቤት ማገር፡፡›› ሲሉ ይቀኛሉ።

በጨዋታው ሁለቱ ቡድኖች በቃላት አማካኝነት ይበሻሸቃሉ፡፡ በገና ጨዋታ ወቅት የተሰደበው የባላባት ወይም የፊት አውራሪ ልጅ ቢኾንም ቂም አይዝም። ተሳዳቢውም ያሻውን ተናግሮ ይሄዳል። ሆድ ያባውም፣ ነገር ያቄመውም እንዲሁ ያሻውን ይናገራል፡፡ በመጨረሻም ሁሉም ተሳስሞ፣ አብሮ በልቶና ጠጥቶ ይለያያል።

ባላባቶች እና የጦር መሪዎች መንጃቸውን አውርደው ይጫወቱ እንደ ነበር ባለሙያው አስታውሰዋል፤ እነዚህ የተከበሩ ሰዎች በጨዋታው ቢሰደቡ ወይም ቢፈነከቱ ቂም ቁርሾ አይዙም፤ለበቀል ሴራ መጎንጎን ብሎ ነገር በፍጹም አይታሰብም ብለዋል፡፡

“እናም” አሉ የባሕል እሴቶች ባለሙያ “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ! ” ይህ ትውልድ መቻቻልን እና ትዕግስትን አጥብቆ ሊማርበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

አቶ እንዳለው ጋሻው የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪ ሲኾኑ የአቶ ደርበውን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ በደብረ ታቦር እና በአካባቢው የሚደረገው የገና ጨዋታ መቻቻል የነገሰበት ነው ባይ ናቸው፡፡በጨዋታው አደጋ ቢፈጠር ቂም አይያዝምና ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

ዘመናዊው የገና ጨዋታስ እንዴት ይከናወን ይኾን?

በአማራ ክልል የባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምንይችል ሙጨ እንዳሉት የገና ጨዋታ ዕድገት በማሳየቱ ጨዋታው ባሕላዊ ይዘቱን ሳይለቅ እንዲከናወን ሕግና ደንብ ተዘጋጅቶለታል ብለዋል፡፡

እንደ ኀላፊው ማብራሪያ የጨዋታው ሜዳ ቁመቱ 100 ሜትር ስፋቱ ደግሞ 90 ሜትር እንዲኾን ተደንግጓል ብለዋል፡፡ የማዕዘን መምቻው ክልልም በኖራ ይሰመራል፡፡

በዚህ ሜዳ ውስጥ ለመጫወት ሁለቱ ተጋጣሚ ቡድኖች 15 ተጫዋቾችን ያቀርባሉ፡፡ 10ሩ ሜዳ ውስጥ ገብተው የሚጫወቱ ሲኾኑ አምስቱ ተቀያሪዎች ናቸው፡፡

የቡድኑ አሰላለፍ እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ሁሉ ግብ ጠባቂ፣ ተከላካይ እና አጥቂ ተጫዋቾች ይኖሩታል፡፡

ጨዋታውን የሚመራ ዋና ፣ የመስመር እዲሁም ተቀያሪ ተጫዋቾችን የሚቀይሩ ዳኞችም ይመደቡለታል፡፡

የሩሯ ክብደት እስከ 500 ግራም ከሚመዝን እንጨት፤ ከጠፍር ወይም ከፕላስቲክ ይዘጋጃል፡፡ የገናው ቁመት ከአንድ ሜትር መብለጥ የለበትም፡፡ ተጨዋቾቹ እኩል ቁመት ያለው የገና ዱላ እንዲይዙ ይገደዳሉ፡፡

ጨዋታው ሲጀመር ሁሉም ተጫዋቾች ተነፋነፍ የሚባለውን ባሕላዊ ልብስ ለብሰው ቦታ ቦታቸውን ይይዛሉ፡፡

በጨዋታው ሕግ መሰረት ሩሯን በእግር እና በእጅ መንካት ነጥብ ያስቀንሳል፡፡ የጨዋታው የጊዜ ርዝማኔ 60 ደቂቃ ነው፡፡ 10 ደቂቃ ረፍት ይሰጣል፡፡

ጨዋታው ለዋንጫ ወይም ለደረጃ ከኾነ ቡድኖቹ ካልተሸናነፉ ተጨማሪ ደቂቃ እዲጫወቱ ይደረጋል፡፡ በዚህም ካልተሸናነፉ የቅጣት ምት እየተሰጣቸው እስኪ ሸናነፉ ድረስ ይጫወታሉ፡፡

የገና ጨዋታን የገና በዓል በሚከበርበት ወቅት ብቻ ከመጫወት ወጥቶ ልክ እንደ እግር ኳስ መዘውተር ቢችል እንደሚጠቅም ያላቸውን ምልከታ ኀላፊው አጋርተዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቋሪት እና የአዴት ወረዳዎች አሥተዳደሮች እና ነዋሪዎች ለመከላከያ ሠራዊት የእርድ እንስሳት እና የገንዘብ ድጋፍ አበረከቱ።
Next articleበ23ኛው ዱባይ ማራቶን በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸነፉ።