የቅዱስ ላሊበላ የልደት በዓል በሰላም እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ገለጹ፡፡

48

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ ታኅሳስ 29 ቀን በድምቀት የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ከአራት ዓመት አንድ ጊዜ ታኅሳስ 28 ቀን ይከበራል።

በኢትዮጵያዊያን የዘመን ስሌት ዘመነ ዮሐንስ ወርሃ ጳጉሜን 6 ቀን መኾኗን ተከትሎ ታኅሳስ 28 ቀን የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡ የልደት በዓል በተለየ ሁኔታ ከሚከበርባቸው አካባቢዎች አንዱ የኾነው ላሊበላ በዓሉ በድምቀት ተከብሯል።

ከዛሬ ምሽት ጀምሮ ደግሞ ደበረ ሮሃ የቅዱሷንም የንጉሷንም የልደት በዓል ዋዜማ ቤዛ ኩሉ ይጀመራል፡፡

የቅዱስ ላሊበላ ልደት ታህሳስ 29 በቤዛ ኩሉ በድምቀት ይከበራል፡፡ የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር በዓሉ በሰላም እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል፡፡

የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወንድምነው ወዳጅ እንዳሉት ባለፉት አምስት ዓመታት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነት እና አሁንም በክልሉ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት የቱሪዝም ዘርፉ ተቀዛቅዞ ቆይቷል፡፡ በከተማ አሥተዳደሩ ከቱሪዝም ዘርፉ በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የነበሩ ተቋማት እና ግለሰቦች በእጅጉ ተጎድተዋል፡፡

አሁን ላይ በተፈጠረው ሰላም በአካባቢው የሚከበረውን ሃይማኖታዊ ትውፊት ለማስቀጠል እና የተዳከመውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ በዓሉን በድምቀት እንዲከበር እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የፀጥታ መዋቅሩ ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት የሰላም እና ደኅንነት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን ነግረውናል፡፡

በርካታ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ያነሱት ከንቲባው ማኅበረሰቡም በተለመደው ጨዋነት እንግዶችን እየተቀበለ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡ በዓሉ በሰላም እንዲከበር አሁንም ማኅበረሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ታህሳስ 29 በላሊበላ ለሚከበረው የቅዱስ ላሊበላ የልደት በዓል በሰላም እንዲከበር የቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የቅዱስ ላሊበላ ልደት በቤዛ ኩሉ በሚከናወነው የካህናት ዝማሬ የዓለምን ትኩረት የሚስብ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

በበዓሉ በየዓመቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች እንደሚታደሙ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

ዘገጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዞኑ ሕዝብ እና አመራር ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመኾን ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል” የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር
Next articleበወልድያ ከተማ ከ900 በላይ የሚኾኑ አረጋውያን እና አቅመ ደካሞች የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ ተጋርተዋል፡፡