“የዞኑ ሕዝብ እና አመራር ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመኾን ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል” የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር

22

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ በዓሉን ከሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር ለማሳለፍ ለሠራዊቱ የእርድ እንስሳት ድጋፍ አድርጓል።

የደቡብ ወሎ ዞን በዞኑ ባሉ ሁሉም ወረዳዎች አመራሩን እና ሕዝቡን በማስተባበር ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ተከታታይ እና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ተነግሯል።

ድጋፉን ያስረከቡት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን፤ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ብር በማሰባሰብ ከ13 በላይ የእርድ ሠንጋዎችን እና 30 የሚጠጉ ፍየሎች ማስረከባቸውን ተናግረዋል።

ዋና አሥተዳዳሪው አክለውም “የዞኑ ሕዝብ እና አመራር ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመኾን ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል”ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በመወከል ድጋፉን የተቀበሉት የ801ኛ ኮር አዛዥ ኮሮኔል አዲሱ በድሩ “የተደረገልን ድጋፍ ሠራዊቱ እንደ ከዚህ ቀደሙ ግዳጁን በሚገባ እንዲወጣ ለሠራዊቱ ትልቅ ስንቅ ነው” ብለዋል።

ኮሎኔል አዲሱ “እኛ በሕዝብ እናምናለን ሕዝቡ እና አመራሩ ያደረጉት ድጋፍ ለሠራዊቱ ትልቅ ሞራል ስለኾነ አሁንም የሕዝቡ ደጀንነት እና ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አልጠራጠርም” ብለዋል።

በተለይ የኮማንድ ፖስታ ከታወጀ ወዲህ ሕዝቡ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ታላቅ መስዋእትነት እየከፈለ መኾኑን ተናግረዋል።

የዞኑን ሕዝብ እና አመራር በማስተባበር መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተጠቁሟል ።

ዘጋቢ:- ደምስ አረጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በተለያዩ የዓለም ሀገራት በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡
Next articleየቅዱስ ላሊበላ የልደት በዓል በሰላም እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ገለጹ፡፡