“ሁሉም ነገር ያለምሳሌ አልተሠራም” የበገና መምህሩ ዲያቆን አይቶልኝ አሞኘ

31

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በገና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያው የማመስገኛ መሣሪያ ነው፡፡

በገና ብዙዎች በአደባባይ በዓላት እና በዐቢይ ጾም የሚደረደረው አድርገው ይወስዳሉ ይሁን እንጅ በገና በየትኛውም ጊዜ መደርደር የሚቻል የቤተክርስቲያን የማመስገኛ መሣሪያ ነው፡፡
የበገና መምህሩ ዲያቆን አይቶልኝ አሞኘ ለአሚኮ እንዳሉት በገና አመጣጡ ሰማያዊ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

በተለይም በራዕይ ዮሐንስ ላይ እንደተቀመጠው “በገና የሚደረድሩ አየሁ” ይላል በመኾኑም በበገና ማመስገን የተጀመረው ከዚያ ወዲህ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

በገና በተለይም በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት መላዕክት ከሰማያት ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም መወለዱን እያመሰጠሩ ያመሠግኑበት እንደነበር ነው ያስገነዘቡት፡፡

ከኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ጋር ተያይዞም የሰው ልጅ ከመላዕክት ባገኘው እውቀት በገናን ለማመስገኛ ሲጠቀምበት ይስተዋላል፡፡

ብዙ ጊዜ የበገና መሣሪያ በዐቢይ ጾም እና በአደባባይ በዓላት ወቅት እንደሚደረደር ቢታወቅም በልደት በዓልም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ከወደቁበት የሀጢያት ቀንበር ለማላቀቅ ሲል ወደ ምድር መምጣቱን እንደሰው ድኾ አድጎ እንዳዳነው እየተሜሰጠረ እንደሚደረደር ነግረውናል፡፡

በገና በተለይም በልደት በዓል ላይ በድንግልና ለወለደችው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምም ያላትን ክብር እና ቅድስና እያሜሰጠሩ እንደሚያመሠግኑም አስገንዝበዋል፡፡

በገናን እድሜው ከሰባት ዓመት ጀምሮ ያለ ሁሉ ሊደረድረው እንደሚችልና የተለያየ መጠን እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ቁመት ሊኖረው እንደሚችልም ነው የገለጹት፡፡

በገና ብዙ ምስጢራትን እንደያዘ የሚናገሩት የበገና መምህሩ ሁለት ቋሚ እንጨቶቹ የሀዲስ እና ብሉይ ኪዳን ምሳሌዎች እንደኾኑ አስረድተዋል። በዘንጎቹ ጫፍ ላይም የስቅለቱ ምልክት መስቀል እንደሚደረግበት ነው የነገሩን።

በገና 10 አውታሮች እንዲኖሩት የተደረገው እንዲሁ ሳይኾን የ10ቱ ቃላትን ለማሜስጠር እንደኾነም ነው ያብራሩት።

በገናው ላይ ያለው ሳጥን ምሳሌ ኢየሱስን በንጽህና እና በድንግልና የወለደችውን ድንግል ማርያምን እንደሚወክልም አስረድተዋል። “ሁሉም ነገር ያለምሳሌ አልተሠራም” የሚሉት የበገና መምህሩ ዲያቆን አይቶልኝ አሞኘ እያንዳንዱ የበገና ክፍል ያለምክንያት እንዳልተቀመጠም ነው የሚገልጹት።

በዓሉ የሰላም እንዲኾን የተመኙት መምህሩ ሁሉም በገናን በመማር በሄደበት ሁሉ ሀገሩን እንዲያስተዋውቅ ጋብዘዋል።

በምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢየሱስ ክርሰቶስ የልደት በዓል በላሊበላ።
Next articleየኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በተለያዩ የዓለም ሀገራት በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡