የፖሊሲ እና የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ማድረጉን አብን አስታወቀ፡፡

683

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የካቲት 14 እና 15 በደብረ ብርሃን ከተማ ያደረገውን መዋቅራዊ ሽግሽግ እንዲሁም የፖሊሲ እና ስትራቴጅ ማሻሻያ ተከትሎ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
አብን መደበኛ ጉባኤው ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከል የምክር ቤት ስያሜውን ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴነት በመቀየር አባላቱንም ከ59 ወደ 50 ዝቅ ማድረጉ ይገኝበታል፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩትን 13 የሥራ አስፈጻሚ አባላትም ወደ 9 ዝቅ ማድረጉን ነው ንቅናቄው የገለጸው፡፡ ይህም አሠራሮችን ምቹ ለማድረግ የተወሰደ እርምጃ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ይታይ የነበረውን የሥልጣን ማሸጋገር ችግር ታሪክ ሊቀይር በሚችል አኳኋን መሪዎቹ ሥልጣናቸውን ለተተኪ በማስረከብ ምሳሌ መሆን እንደቻሉም አመላክቷል፡፡ የቀድሞው የአብን ሊቀመንበር ደሳለኝ ጫኔ (ዶክተር)በፓርቲው የነበራቸው የሥልጣን ጊዜ መልካም እንደነበረ ጠቅሰው በዛሬው መግለጫ ላይ አመስግነዋል፡፡
በሌላ በኩል የታሰሩ መሪዎቹን ለማስለቀቀ አብን ጠርቶት የነበረው የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ መንግስት ባሳየው በጎ ምላሽ መቅረቱን አብን አስታውቋል፡፡ የአብን የፖለቲካ አደረጃጀት እና ትግል በአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ ላይ እንጅ በሚፈጠር ድንገተኛ ክስተት ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ ጥያቄው ምላሽ እስኪያገኝ ትግሉ እንደሚቀጥልም ንቅናቄው በመግለጫው አስታውቋል፡፡ አባላቱ እና ደጋፊዎቹ የሚያደርጉት ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርቧል፡፡

አብን የፖሊሲ እና የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ አድርጓል ያለው ንቅናቄው ይህም አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ያደረገውን የፖሊሲ ማሻሻያ ተከትሎ የተሰራ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ የሕዳሴ ግድብ በተመለከተ እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚደረገው ግንኙነት መዋቅሩን የጠበቀ ሊሆን እንደሚገባም በመግለጫው አመላክቷል፡፡
የድርጅቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ ከአባላት እና ደጋፊዎቹ ጋር እንደሚገናኙም አመልክቷል፡፡
ዘጋቢ፡-አንዱዓለም መናን-ከአዲስ አበባ

Previous article“መንግሥት በተወዛወዘ ቁጥር የማይወዛወዝ አቋም ሊኖረን ይገባል፡፡” የአማራ ክልል የሴቶች ማኅበር
Next articleየከባድ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ሰዓት ማሻሻያ ተደረገበት፡፡