
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከኢትዮጵያውያን የግብረገብ አሴቶች ውስጥ የመረዳዳት ባሕል አንዱ ነው። በተለይም ደግሞ በሞት፣ በህመም፣ አደጋ ላይ የወደቁትን እና አቅመ ዳካሞችን የመርዳት ባሕሉ የጎላ ነው።
የመረዳዳት እሴቱ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮችን የመፍታት ድርሻው የጎላ ቢኾንም በሚፈለገው ልክ እና ዓይነት ዳብሯል ማለት ግን አይቻልም።
የመረዳዳት እሴቱ ከግብረ ገብ እሴትነቱ ባለፈ ሃይማኖታዊ መሠረቱ ከፍተኛ እንደኾነ የባሕር ዳር ርዕሰ ከተማ ወረዳ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ መልዓከ ሰላም ለዓለም ጌታሁን ነግረውናል።
መልዓከ ሰላም ለዓለም እንዳሉት ያለው ለሌለው ወይም ለአቅመ ደካሞች ማካፈል እንደሚገባ ሃይማኖታዊ አስተምህሮው ያዛል።
“ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ አንዲት ጻዲቀ መበለት የምትሰጠው ብታጣ ሙሬ ሸምጥጣ በመጋገር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለነበሩ ድሆች ሰጠች። ኢየሱስ ክርስቶስም ሌሎች ካላቸው ይዘው ሲመጡ አንች ግን የሌለሽን ይዘሽ መጥተሻልና እስከ ዓለም ፍፃሜ ሲነገር ይኖራል'” እንዳለው አስተምህሮ አሁንም እየተነሳ ይገኛል ብለዋል።
“ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጥም፣ የሚቀበልም ጌታ በመኾኑ ከሃብታሞች ጋር አድሮ ይሰጣል። ከድሆች ጋር ኾኖም ይቀበላል” ብለዋል።
በበረት የተወለደው የወደቀውን ሰው ለማንሳት በመኾኑ በዓሉን ለሌለው በማካፈል ማክበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከዚህ በፊት አባቶቻችን ቀድመው ወተት በማጠራቀም ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ ለአቅመ ደካሞች ይሰጡ ነበር። ቅርጫ ስጋም ጭምር በማካፈል በዓሉን በቤታቸው፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር እንዲኹም በየአብያተ ክርስቲያናቱ በጋራ እንዲያሳልፉ ይደረግ እንደነበር ገልጸዋል።
አሁን ላይም የመረዳዳት እሴቱ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ቢኖርም ከዚህ በተሻለ መንገድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የሃይማኖቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ ድሆችን በማገዝ፣ ለሀገራቸው እና ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም በጸሎት በማሰብ ሊኾን እንደሚገባም መክረዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!