“በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የተጣላ ይታረቅ፤ የተለያዬ ይገናኝ” መጋቤ ብሉይ ዳኛው አከላት

43

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)መጋቤ ብሉይ ዳኛው አከላት የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በነቢያት ትንቢት በተስፋ ሲጠበቅ የነበረ ለሰው ልጅ ድኅነት ወሳኙ ክስተት ነው ብለዋል።

አዳም እና ሔዋን እጸ በለሥን በልተው ከገነት ከወጡ ጊዜ ጀምሮ ሰው እና እግዚአብሔር በቦታ እና በአስተሳሰብ ተለያይተው ስለመቆየታቸው መጋቤ ብሉይ ዳኛው አከላት ይናገራሉ፡፡

በዓሉን አስመልክተው ሲናገሩም በናፍቆት ሲጠበቅ የቆየው የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ነው ብለዋል፡፡

አዳም እና ሔዋን እጸ በለስን በልተው ከገነት በተባረሩ ጊዜ አጥብቀው አዝነው ተክዘውም ነበር ይላሉ፡፡ ሃዘናቸውን የተመለከተው እግዚአብሔር ከልጅ ልጃችሁ ተወልጄ አድናችኋለው የሚል የተስፋ ቃል እንደሰጣቸው ያብራራሉ፡፡

ይህን የክርስቶስ ቃል መላዕክት ሰምተዋል የሚሉት መጋቤ ብሉይ ዳኛው የሰሙት መላዕክት ለነቢያት ነገሯቸው ነው ያሉት፡፡

ትንቢት የተነገረለት፤ ሱባኤ የተቆጠረለት ኢየሱስ ክርሥቶስ አዳምን ከፍዳ እና ከመከራ ያድነው ዘንድ በሥጋ ተወለደም ብለዋል፡፡

እወለዳለሁ ብሎ ስለመወለዱ የተናገረው አምላክ መቼ እንደሚወለድ እና ከማን እንደሚወለድ አስቀድሞ የተናገረው ክርሥቶስ ቃሉ ይፈጸም ዘንድ በሥጋ ተገለጠ፡፡

የተናገረው 5 ሺህ 500 ዘመን ሲፈጸምም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ልክ በዛሬው ቀን ከተወለደ እነኾ ዛሬ 2016 ዓ.ም ሞላው ብለዋል፡፡

በዓሉን ለማክበር ብዙ ምክንያት አሉት ያሉን መጋቤ ብሉይ ዳኛው በዓሉ የሚከበረው የሁሉም በዓል መጀመሪያ እና የበዓላት ሁሉ ራስ በመኾኑ ነው ብለውናል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ተሠቀለ፣ ሞተ፣ ተነሣ እና ዐረገ ለማለት መጀመሪያ ተወለደ ማለት የግድ ሥለኾነ ይህን በዓል የበዓላት ሁሉ ራስ እንደሚያደርገው አስገንዝበዋል፡፡

ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት ትንቢት ተነግሮለታል ሱባኤ ተቆጥሮለታል፡፡ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ልክ በዛሬው ቀን በሥጋ ተገለጠ፡፡ የኢየሱስ መወለድ የሰው ልጅ አዲስ ምዕራፍ እንዲጀምር እንዳደረገውም ተናግረዋል፡፡

የሉቃስ ወንጌልን ጠቅሰው “ለእግዚአብሔር ምሥጋና ይገባል በምድርም ሰላም” ብለው መላዕክት አመሥግነዋል፤ ይህም የተለያየውን ዓለም አንድ አደረገው ሲሉ ያስረዳሉ።

ኢየሱስ ሲወለድ ሦስት ነገሥታት ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤ ለማበርከት የመጡት ከሩቅ ምሥራቅ እና ከኢየሩሳሌም ቢኾንም በአንድነት ምሥጋና ስለማቅረባቸው በመግለጽ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የጥል ግድግዳን እንዳፈረሰ ነግረውናል፡፡

ተለያይተው የነበሩ አካላት በአንድነት የዘመሩበት፣ የጠፋው ሰላም የተገኘበት፣ ሰው ወደ ኢየሱስ የቀረበበት፣ ተጣልተው የነበሩ የታረቁበት እና ሥጦታ ያቀረቡበት በዓል በመኾኑ ትልቅ በዓል እንደኾነ አስረድተዋል። በዓሉ ሲከበር የተጣላ ይታረቃል፣ የተራራቀ ይገናኛልም ብለዋል መጋቤ ብሉይ ዳኛው፡፡

“ዛሬ በኢየሱስ ልደት የተጣላ ይታረቅ፤ የተለያዬ ይገናኝ፤ ተለያይተው የነበሩ ወንድማማቾች ወደ አንድ ይምጡ” የመጋቤ ብሉይ ዳኛው አከላት መልዕክት ነው።

በምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በተለያዩ የዓለም ሀገራት በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች እየተከበረ ነው።
Next article“በዓሉን ስናከብር ድሆችን በማገዝ፣ ለሀገራችን እና ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም በጸሎት በማሰብ ሊኾን ይገባል” መልዓከ ሰላም ለዓለም ጌታሁን