የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በተለያዩ የዓለም ሀገራት በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች እየተከበረ ነው።

21

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች እና ልዩ ልዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።

የጁሊያን ዘመን አቆጣጠርን የሚከተሉ የምሥራቅ እና ኦሬንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያናት የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በድምቀት እያከበሩ ይገኛሉ።

በዓሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአርመን፣ በሩስያ፣ በግብጽ፣ በቤላሩስ፣ በጆርጅያ፣ በካዛኪስታን፣ በሞልዶቫ፣ በሞንቴነግሮ፣ በሰርቢያ እና በሰሜን መቄዶንያ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች እየተከበረ ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስትያንም በፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ መሪነት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በዓሉን አስመልክቶ ሥርዓተ ቅዳሴ መካሄዱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳምም የልደት በዓል በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

የጁሊያን የዘመን አቆጣጠር በምትከተለው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያንም እንዲሁ የሞስኮ እና የመላው ሩሲያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ክሪል እና ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በተገኙበት መከበሩ ተዘግቧል።

በተመሳሳይ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ዳግማዊ በመሩት ሥርዓተ ቅዳሴ ተከብሯል።

በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያንም እንዲሁ በዓሉ በስርዓተ ቅዳሴ የተከበረ ሲሆን ምዕመናን ስጦታ በመለዋወጥ እያከበሩት እንደሚገኙ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አከባበር እና የስጋ ቅርጫ፡፡
Next article“በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የተጣላ ይታረቅ፤ የተለያዬ ይገናኝ” መጋቤ ብሉይ ዳኛው አከላት