የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አከባበር እና የስጋ ቅርጫ፡፡

35

ቅርጫ በስፋት ከሚከወንባቸው በዓላት መካከል የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አንዱ ነው። በበዓሉ ሰዎች በየአካባቢያቸው ተሰባስበው እንደየ አቅማቸው የእርድ በሬ በመግዛት አርደው ይከፋፈላሉ።

አቶ እያያ እያሱ በደብረ ታቦር ከተማ ይኖራሉ። ፊሪዳ አርደው በማቃረጥ ተጨማሪ ገቢ ያገኛሉ። ላለፉት 12 ዓመታት የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ጨምሮ ስጋ በማረድ ያቃርጣሉ። በበዓላት የፍሪዳ ግዥ ክዋኔን፣ የቅርጫን ልማድን እና የማኅበረሰብ እሴትን አጫውተውናል።

በዓመት በዓል በተለይም እንስሳት በሚደልቡበት የመኸር ወቅት እርድ እንደሚበዛ የተናገሩት አቶ እያያ በልደት ስጋ ለመቃረጥ አስቀድሞ የከብትን መድለብ የሚያውቁ እና ፈቃደኛ የኾኑ ሰዎችን በአስተባባሪነት በማካተት እንደሚጀመር ገልጸዋል። ከቅርጫው ቀን አስቀድሞ ሰዎች እንደቅርበታቸው እና ትውውቃቸው በመሰባሰብ የእርድ ከብቱን ለመግዛት ገንዘብ ያዋጣሉ። አልፎ አልፎ ደግሞ ፈቃደኛ ግለሰቦች ከብቱን በራሳቸው ገንዘብ ገዝተው በኋላ ላይ ገንዘቡን ከተቃራጮች የሚሰበስቡም እንዳሉ ነግረውናል። እርሳቸውም ገንዘብ ከተቃራጮች የሚሰበስቡት ስጋውን ካከፋፈሉ በኋላ መኾኑን በአብነት ነግረውናል።

እንደ አቶ እያያ ገንዘቡን አዋጥተው እና ተሰባስበው ገበያ በመሄድ ስጋ አዋቂዎች እንዲገዙ ኀላፊነት የሚሰጡም አሉ። የኾነ ኾኖ የስጋ ሽንጥ፣ ብልት እና አወራረድ የሚያውቅ ሰው በእርድ ከብቱ ግዢም ኾነ በእርድ ጊዜ ተፈላጊ መኾኑን ነው አቶ እያያ የሚናገሩት።

በቀድሞው ልማድ የግዢውን ወጪዎች እኩል እና ዕለቱን አምጡ እንደማይባል እና ከእጃቸው ገንዘብ የሌላቸው ቀስ ብለው የሚከፍሉበት የመተሳሰብ እና የመረዳዳት ባሕል እንደነበር ያስታውሳሉ።

በስጋ ክፍፍል በኩልም በከተማ አንድን ፊሪዳ ለስምንት የመካፈል እና ግማሽ እና ሩብ መደብም መያዝ ይቻላል። በገጠሩ ግን አንድን ፊሪዳ እስከ 20 የሚደርሱ ሰዎች እንደየአቅማቸው ሙሉ መደብም ኾነ ግማሽ መደብ ስጋ እንደሚወስዱ ነው አቶ እያያ የነገሩን።

ቀደም ባሉ ጊዜያት የተሻለ ሃብት ያላቸው ሰዎች አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ወጪ በመሸፈን ሲያገኙ የሚከፍሉበት ልማድም እንደነበር ያስታወሱት አቶ እያያ ዛሬ ላይ ግን ይኽ የመተሳሰብ ባሕል እየቀነሰ መኾኑን ገልጸዋል።
ሰዎች ስጋ እንደሚፈልጉ በመረዳት በሬ ገዝተው አርደው፣ ስጋውን መድበው እና ዋጋ ተምነው የሚያከፋፍሉም እንዳሉ አቶ እያያ ነግረውናል። በዚህም የስጋውን ዋጋ ዕለቱን መክፈል ለማይችል ሰው ሲያገኝ ሊከፍል ከቅርጫው እንዲሳተፍ ይፈቀድለታል።

ፊሪዳ አርዶ ስጋ በመቃረጥ ሂደት ከእርድ ከብት ግዢ እስከ ስጋ ክፍፍል ድረስ ሁሉም በቻለው መጠን በሥራ መረዳዳት እንጂ ክፍያ የሚጠየቅበት እንዳልነበር ያስታውሳሉ። ፊሪዳውን በመግዛት፣ በመንዳት፣ በማረድ፣ ስጋውን ከፋፍሎ በመመደብ ለአዛውንት እና አቅመ ደካሞች ስጋውን ቤታቸው በማድረስ መተሳሰብ የተሞላበት እንደነበር ገልጸዋል። በሂደት ግን መተሳሰቡ መቀዛቀዝ እንደሚታይበት ተናግረዋል።

”ሰንበር ምላስ” እና ”ኩርሽ ሙርሽ” በመባል የሚታወቁትን የስጋ ክፍሎች እዚያው እርድ እና ቅርጫው ቦታ ላይ ጠባብሶ በጋራ መመገብ ሌላው እርድ እና ቅርጫን ልዩ የሚያደርገው ተወዳጅ ክዋኔ ነው።
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የስጋ ቅርጫ ሥርዓት እና ትውፊት የቀደመው የመተሳሰብ፣ የመሰባሰብ እና የመደጋገፍ እሴቱ እየተሸረሸረ ቢኾንም ባሕሉ ግን አሁንም ቀጥሏል። በገጠሩ ግን በአንጻሩ የቀድሞ ልማዱን የማስቀጠሉ ሁኔታ እንዳለ ነው የነገሩን።

የገንዘብ አቅም ካላነሰ በስተቀር በቤት በግ ቢታረድም ለቁርጥ እና ለጥብስ የቅርጫ ስጋ አይቀሬነት የልደት በዓል የስጋ ቅርጫ አንዱ መገለጫ እንደኾነም አቶ እያያ ይናገራሉ።

የደለበውን የእርድ ከብት መርጦ፣ ዋጋ ተከራክሮ በመግዛት፣ አርዶ፣ ስጋውን በብልት በብልቱ ለይቶ በፍትሃዊነት የሚያከፋፍል ሰው ‘ጥሩ ስጋ አበላን’ በሚል እንደሚመሰገን እና ለወደፊቱ የፊሪዳ ቅርጫም ተፈላጊ እንደኾነ ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት የወንጌል ክፍል ኀላፊ ሊቀ ጉባኤ መጋቢ ሳሙኤል እንየው በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ወቅት የሚከወነው የቅርጫ ሥርዓት ከሃይማኖቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባይኖረውም ሰዎች ማኅበራዊ ትስስራቸውን ለማጠናከር የሚከውኑት ተግባር እንደኾነ ገልጸዋል።

”ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው የተጨነቁትን ለማረጋጋት፤ ያዘኑትን ለማጽናናት፤ በሰውና በእግዚአብሔር፣ በሰው እና በመላእክት መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳን ለማፍረስ ስለኾነ ኅብረተሰቡ ይህንን እያሰበ በዓሉን በደስታ እንዲፈጽም” አሳስበዋል።

”ጓደኛ እየተራበ እና እየተጠማ፤ ወገንም እየተቸገረ ደስታ የለም” ያሉት መጋቢ ሳሙኤል ኅብረተሰቡ በበዓሉ ሲደሰት የተቸገሩ ወገኖቹን ሳይዘነጋ እንዲኾንም አሳስበዋል።

በአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል እሴቶች ባለሙያ ደርበው ጥላሁን እርድ እና ቅርጫ የበዓላት ኅብረተሰባዊ ልማዶች መኾናቸውን ነው የተናገሩት።

በማንኛውም በዓላት ወቅት ማኅበረሰቡ ደስታውን ከሚገልጽባቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ እርድ መፈጸም እንደኾነ የገለጹት አቶ ደርበው የስጋ ቅርጫ ቤተሰብን ለማስደሰት ታስቦበት የሚዘጋጅ ነው ብለዋል።

አቶ ደርበው በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሚፈጸመው እርድ እና ቅርጫ ማኅበራዊ እኩልነትን ለማስቀጠል ጠቃሚ እንደኾነ ገልጸዋል። ስጋው እኩል ተመድቦ በእጣ መከፋፈሉም ፍትሃዊነትን ይዘክራል፤ አምና አብሮ የነበረ ሰው ‘ዘንድሮ ምን ኾኖ ቀረ?’ ተብሎ ሽማግሌ የሚላክበት ማኅበራዊ ግንኙነትን የሚያጠናክር የሕዝብ እሴት ነውም ብለዋል።

‘አብረን ዋልን፤ አብረን በላን፤ አብረን ተደሰትን፤ አልተለያየንም፤ ማንም ከማንም አላነሰም’ በሚል የሚፈጥረው የሥነ ልቦና እርካታም ከፍተኛ መኾኑን ጠቅሰዋል።

”የቅርጫ ሥነ ሥርዓቱ ሌላኛው ጠቃሚ ነገር ያላቸው የሌላቸውን አግዘው በዓልን በደስታ እንዲያከብሩ ማድረጉ ነው” ይላሉ የባሕል ጥናት ባለሙያው።

በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በነበረው የጣሊያን ወረራ ማግስት በኢትዮጵያ የእንስሳት በሽታ ከብቱን ሁሉ ፈጀው፤ ንጉስ ምኒልክ ከሐረር ገዢው ራስ መኮነን ግዛት የተላኩላቸውን 5 ሺህ በሬ እና 5 ሺህ ላሞች እንዳይታረዱ ደነገጉ። ከጾምን በኋላ በምን እንግደፍ የሚል ጥያቄ ከኅብረተሰቡ ሲቀርብባቸውም በሬ አርዶ በቅርጫ እንዲከፋፈል ማዘዛቸውን ጳውሎስ ኞኞ በ ‘አጤ ምኒልክ’ የታሪክ መጽሐፋቸው መጥቀሳቸውንም አቶ ደርበው አንስተዋል። ይህ ታሪክም ለዛሬ ዘመኑ ቅርጫ እንደመነሻ እንደኾነ ይታመናልም ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

Previous article“የሰው ተኮር ማኅበራዊ አገልግሎት ሥራዎችን እጅ ለእጅ ተያይዘን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንሠራለን” የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
Next articleየኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በተለያዩ የዓለም ሀገራት በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች እየተከበረ ነው።