
አዲስ አበባ: ታኅሳስ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 የአቅመ ደካሞችን ቤት አድሶ ለባለቤቶቹ አስረክቧል። የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአራዳ ክፍለ ከተማ ለአራት አቅመ ደካማ ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው ባለ ሁለት ክፍል የመኖሪያ ቤት እድሳትን አጠናቆ ከነሙሉ የቤት እቃው አስረክቧል፡፡
የቤት እድሳት ለተደረገላቸው አቅመ ደካማ ቤተሰቦች ርክክብ ያደረጉት የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል። ከእነዚህም መካከል የምገባ እና የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ ሥራዎች ተጠቃሽ መኾናቸውን አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ካለው ውስን ሃብት አብቃቅቶ አራት ቤቶችን አድሶ ለባለቤቶቹ አስረክቧል ብለዋል። ይህ የሰው ተኮር ማኅበራዊ አገልግሎት በዚህ የሚቆም ሳይኾን ወደፊትም እጅ ለእጅ ተያይዘን ቀጣይ የልማት ሥራዎችን እንሠራለን ሲሉ ተናግረዋል። አፈ ጉባኤው በሥራው ለተሳተፉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።
የቤት እድሳት የተደረገላቸው ሦስት እናቶች እና አንድ አባት አቅመ ደካማዎች መኾናቸውን የገለጹት የወረዳው ሥራ አስፈጻሚ ታደሰ አድኖ ናቸው። ሥራ አስፈጻሚው “የሰው ተኮር ተግባራችንን በመቀጠል 25 ቤቶችን ለማደስ አቅደን እየሠራን ነው” ብለዋል። እድሳት የተደርገላቸውን ቤቶች የተረከቡት አቅመ ደካሞች እኛ አሁን ባለን አቅም ቤታችንን ለማደስ ቀርቶ የእለት ኑሯችንንም ለመምራት የማንችል በመኾናችን የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ወረዳው ላደረገልን ድጋፍ ከልብ እናመሠግናለን ብለዋል፡፡ ቤታችን በዚህ መልክ ታድሶልን ስንረከብ ዛሬም ሀገር እና ወገን እንዳልረሳን እንዲሰማን አድርጎናል ሲሉ ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የበዓል በግ ሥጦታም ለአቅመ ደካሞቹ ተበርክቷል።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!