
ባሕር ዳር፡ የካቲት 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበር ምክር ቤት በባሕር ዳር ከተማ እየመከረ ነው፡፡
ምክር ቤቱ በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የ6 ወር የሥራ አፈጸም ላይ ነው ከምክር ቤቱ አባላት እና ከተጋባዥ እንግዶች ጋር እየተወያዬ የሚገኘው፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበር ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ ዘርፎች ተጠቃሚ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ሴቶችን 95 በመቶ የተዘዋዋሪ ፈንድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ውስጥ አንዱ መሆኑን የአማራ ክልል የሴቶች ማኅበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ሠላማዊት ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩ እድሜያቸው የገፋ፣ በፊስቱላ እና በሌሎች በሽታዎች ሲሰቃዩ፤ ከማኅበረሰቡ ተገልለው የቆዩ ሴቶች ከበሽታው ነፃ እንዲሆኑ እና እራሳቸውን በኢኮኖሚ ችለው እንዲኖሩ ማድረጉንም ሊቀመንበሯ አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከ20 ዓመታት በላይ እንደመቆየቱ የሚጠበቅበትን ያህል ማኅበሩ አለመሥራቱንም ተናግረዋል፡፡ ከማንኛውም የፖለቲካ ጣልጋ ገብነት ነፃ በማደርግ ለሴቶች መብት እንዲቆም ከነበረው አሠራር ወጥተው እንደሚሠሩም ወይዘሮ ሠላማዊት ተናግረዋል፡፡
በተለይ ከለውጡ ጋር ተያይዞ የአደረጃጀት፣ የአሠራር እና የመመሪያ ለውጥ መደረግ እንዳለበት ሥራ አስፈፃሚው መወያየቱን ሊቀመንበሯ ጠቁመዋል፡፡
የታገቱ ተማሪዎች እንዲለቀቁ ማኅበሩ መግለጫ አውጥቶ እንደነበረ ያስታወሱት ሊቀመንበሯ “እኛ መግለጫ ከማውጣት ባለፈ ለምን ሞጋች ማኅበር አንሆንም? እንደሌላው ያልተደራጀ ሰው ለምን እንሆናለን? ለምን ጠንካራ አቋም ይዘን መንግሥትን አንሞግትም? በማለት ከሥራ አስፈፃሚው ጋር ውይይት አድረገናል’’ ብለዋል፡፡
የማኅበሩ ምክር ቤት ከምክክር በዘለለ ጠንካራ ውይይት እንዲያደርግ አቅጣጫ የሰጡት ወይዘሮ ሠላማዊት “ክልላችን ከገባባቸው ወቅታዊ እና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለማውጣት ከተለመደው አሠራር እና ዝንባሌ ወጥተን መሥት ይጠበቅብናል፣ መንግሥት በተወዛወዘ ቁጥር አብረን መወዛወዝ ሳይሆን የራሳችን አቋም ሊኖረን ይገባል” ሲሉም ከተለመደው አካሄድ መውጣት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ