“ለወገኖቻችን የበዓል መዋያ ድጋፍ ስናደርግ በደስታ ነው” የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ ሥራ አሥኪያጅ ወርቁ ባየ

36

ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ በዓልን ምክንያት በማድረግ በባሕርዳር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ አድርጓል፡፡ ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖችም ስለ ድጋፉ አመሥግነዋል፡፡ ወይዘሮ ወርቄ አሥረስ የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ ለበዓል መዋያ ድጋፍ ያደረገላቸው እናት ናቸው፡፡ “ለበዓል ተዘግተን ነበር የምንውለው፣ በዓሉን አስበው ድጋፍ ስላደረጉልን ውለታውን እርሱ ይክፈላቸው” ብለዋል፡፡ ማጣት እጃቸውን አስሯቸው በዓልን ለማክበር ይቸገሩ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

ሌላኛዋ እናት ኢትዮጵያ ፈረደ “ ዛሬ ጦም አዳሪዎች ይሄን ስናገኝ ደስታችን ልዩ ነው፤ ይሄን ያሰበልን ፈጣሪ ያስብልን፣ እርሱ ይጠብቃቸው” ነው ያሉት፡፡ በመልካም አሳቢ ሰዎች እና ተቋማት እርዳታ ኑሯቸውን እየደጎሙ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ “ምንም አልነበረኝም፣ ፈጣሪ ይስጣቸው ዓመት በዓል አዋሉን” ነው ያሉት፡፡

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ አማራ ፓይፕ ፋብሪካ በማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ሰፋፊ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡ በተለይም በባሕርዳር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን ሲደገፍ መቆየቱን ነው የተናገሩት፡፡ እያደረገው ላለው ድጋፍም አመሥግነዋል፡፡ ሌሎች ተቋማትም ከአማራ ፓይፕ ፋብሪካ ትምህርት በመውሰድ ለወገኖች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የተደረገው ድጋፍ አብሮነትን፣ መደጋገፍን፣ በጋራ መሥራትን ያሳያል ይህ ከኾነ ደግሞ ሁሉንም ነገር መሻገር እንደምንችል የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ የአማራ ባሕል እርስ በእርስ መደጋገፍ ነው ያሉት ኀላፊው የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ እርስ በእርስ ተደጋግፈን ብዙ ነገር ማድረግ እንደምንችል አሳይቶናል ነው ያሉት፡፡

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ንጹሕ ሽፈራው መረዳዳት እና መከባበር የሀገራችን የቆዬ ባሕል ነው ብለዋል፡፡ የቆዬውን ባሕል ለማዳበር ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን መደገፍ አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ካለን ነገር ላይ በማካፈል በዓልን ማሳለፍ የተለመደ ተግባር መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን እንደ እቅድ ይዞ የሚደገፍ ተቋም መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ላደረገው ድጋፍም አመሥግነዋል፡፡

አሁን ያለው የሰላም ሁኔታ አቅመ ደካሞች ተንቀሳቅሰው መሥራት የማይችሉ በመኾናቸው በዓልን ለመዋል እንደሚቸገሩ ነው ያነሱት፡፡ በዓሉ በሰላም እንዲከበር አካባቢን በመጠበቅ እና ልጆችን በመምከር መኾን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት የኑሮ ውድነት መናር አለ፣ በዚህ ደግሞ ቀጥተኛ ተጋላጭ የኾኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ወገኖች ናቸው ብለዋል፡፡ ሁሉም በዓልን ሲያከብር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን በማሰብ ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የመረዳዳት እና የመጠያየቅ ባሕልን ማጎልበት ይገባልም ብለዋል፡፡ ቢሮው ተጋላጭ የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የመደጋገፍ ሥራውን ሁልጊዜም አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ነው ያሉት፡፡ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ማዕድ ማጋራትን እንደ ባሕል አድርጎ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል፡፡

የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ ሥራ አሥኪጅ ወርቁ ባዬ ፋብሪካው የተቋቋመበት ዋና ዓላማ ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር፣ ክልሉ ብሎም ሀገሪቱ በምታደርገው የልማት እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና እንዲጫወት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ነው ብለዋል፡፡ ፋብሪካው በቋሚ እና በጊዜያዊነት ከ500 በላይ ለሚኾኑ ወገኖች የሥራ እድል መፍጠሩንም አመላክተዋል፡፡

ፋብሪካው የዜጎችን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ለማረጋገጥ እና አርሶ አደሮች የተሻሉ ምርቶችን እንዲያመርቱ የሚያግዙ ምርቶችን እንደሚያመርትም ገልጸዋል፡፡ ፋብሪካው ከክልል አልፎ ለሀገሪቱ ምርቶችን እንደሚያቀርብም ተናግረዋል፡፡ ከመደበኛ ሥራው ባሻገር አቅመ ደካማ ወገኖችን እንደሚደግፍም ገልጸዋል፡፡ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን ቤት በመገንባት፣ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ በመስጠት፣ የጤና መድኅን መዋጮ መሸፈን ለማይችሉ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በከተማዋ ከአንድ ሺህ በላይ ለሚኾኑ አቅመ ደካማ ወገኖች የአንድ ዓመት የጤና መድኅን ክፍያ እንዲከፈልላቸው ማድረጉንም አብራርተዋል፡፡

በአነስተኛ እና ጥቃቅን ለተደራጁ ማኀበራት እና ከጦር ሜዳ ለተመለሱ የሠራዊት አባላት ድጋፍ በማድረግ አስተዋጽኦ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የፋብሪካው ሠራተኞች እና መሪዎች በመነጋገር በዓልን ምክንያት በማድረግ በችግር ምክንያት በዓልን ማክበር ለማይችሉ ወገኖች ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

ክልሉ በፈተና ውስጥ መቆየቱን የተናገሩት ሥራ አሥኪያጁ ከሰላሙ መታጣት ጋር የኑሮ ውድነት አስቸጋሪ ኾኗል፤ ፋብሪካው በተቻለው መጠን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችንም ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት፡፡ ለወገኖቻችን የበዓል መዋያ ድጋፍ ስናደርግ በታላቅ ደስታ ነውም ብለዋል፡፡ ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች በሰላም እጦት ችግር የመጀመሪያ ተጠቂዎች መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ ስጦታችን ብዙ ነው ማለታችን ሳይኾን ለመተሳሰብ አስበን ነው እንጂ ነው ያሉት፡፡ ክልሉ ሰላም ሲኾን ከዚህ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ወገኖች የራሳቸውን ገቢ የሚያመነጩበትን ሥራ እንሠራለንም ብለዋል፡፡

አሁን ያለው ሰላም አስተማማኝ እንዲኾን ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“የሰው ተኮር ማኅበራዊ አገልግሎት ሥራዎችን እጅ ለእጅ ተያይዘን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንሠራለን” የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር