“የክርስቶስ ልደት ብዝኀነት፣ እኩልነትና በአንድነት በገሀድ የታዩበት የዓለም ሕዝቦች ምልክት ነው” የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

54

ባሕርዳር: ታኅሳሥ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በክርስቶስ ልደት በብዝኀነት በእኩልነት መኖርንና ለአንድ ዓላማ መኖርን በአንድነት መሰለፍን እንማርበታለን ብለዋል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር።
እኛ ኢትዮጵያዊያን ብዝኀ ማንነት ያለን ሕዝቦች ነን ያሉት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ልዩነታችንን ወደ ጎን በመተው በእኩልነትና በአንድነት ከቆምን በሀገራችን ሰላምን እናሰፍናለን፤ ብልጽግናችንም እናረጋግጣለን ብለዋል፡፡ የክርስቶስ ልደት ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገርን፣ ከኦሪትነት ወደ ሀዲስነት መለወጥን ይነግረናል ነዉ ያሉት፡፡

አፈ ጉባኤው እንዳሉት ለውጥ ከነባር ወደ አዲስና የተሻለ ማንነት መሸጋገር ነው፤ ወደሚያልሙትና ተስፋ ወደሚያደርጉት ነገር ለመድረስ ጉዞ መጀመር ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ጉዞ ላይ ናት ያሉት አቶ አገኘሁ በሰንካላ ምክንያቶች ለውጡ ሳይቀለበስ ከምንመኘውና ከምናልመው ግብ ላይ ለመድረስ፣ ከድህነት ወደ ብልጽግና ለመሸጋገር ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከአሮጌውና ልዩነትን ከሚያቀነቅነው ስሁት ትርክት ወጥተን ወደ አዲስና የጋራ አስተሳሰብ እንድንሸጋገር አደራ እላለሁ ብለዋል፡፡

በክርስቶስ ልደት ለበርካታ ዘመናት የቆየ የጥል ግድግዳ ተደርምሶና የልዩነት አጥር ፈራርሶ በአብሮነትና በፍቅር ሁሉም ዘምረዋልም ነዉ ያሉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤዉ። ጥላቻና ያልተገባ ልዩነት መጠፋፋትን እንጂ መደጋገፍን አያመጣም፤ በመኾኑም በመሀከላችን የተፈጠሩትን ልዩነቶች በውይይትና በንግግር አስወገድን የጋራ እሴቶቻችንን እያጠናከርን መጪውን ጊዜያችንንና የብልጽግና ጉዟችንን እንድናሳምር በራሴና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ስም መልእክቴን ለማስተላለፍ እወዳለሁ ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በዓሉን ስናከብር በኢትዮዽያዊ ጨዋነት እና የመረዳዳት ባሕላችን ሊኾን ይገባል” የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
Next article“እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)