
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ሠራተኞች እና የሥራ ኀላፊዎች የልደት በዓልን አስመልክቶ ከደመወዛቸው በማዋጣት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው እና ለአቅመ ደካሞች ማዕድ አጋርተዋል።
የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) በማዕድ ማጋራቱ ላይ “ከዓለም አቀፍ የገበያ ዝንፈቶች ባለፈ በሀገራችን እና በክልላችን የተከሰተው የሰላም እጦት የነዋሪዎችን የኑሮ ጫና አክብዶታል ብለዋል፡፡ ዶክተር ማማሩ ችግሩን ለመሻገር ከሰላም ማስከበር ባለፈ “የሕዝቡን የመረዳዳት እና የመደጋገፍ እሴት ማስቀጠል ያስፈልጋል” ነው ያሉት። የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች እና የሥራ ኀላፊዎች የዛሬው ተግባርም የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል::
ለ50 በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ እና ለአቅመ ደካሞች የማዕድ ማጋራት ሥነ ሥርዓትም ተከናውኗል። የዳቦ ዱቄት፣ የምግብ ዘይት እና እንቁላል ለእነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማበርከት ተችሏል። የማዕድ ማጋራቱ ተጠቃሚዎች የተቋሙ ሠራተኞች እና የሥራ ኀላፊዎች ለሠሩት መልካም ተግባር አመሥግነዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!