ልደትን በላሊበላ ለማክበር የሚገቡ እንግዶችን እየተቀበሉ ማስተናገድ መጀመራቸውን የላሊበላ ነዋሪዎች ገለጹ።

14

ባሕርዳር: ታኅሳሥ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ላሊበላ የዓለም አይኖች ሁሉ ለማየት የሚናፍቁትን ትልቅ የቱሪዝም ገጸ በረከት አቅፋ የያዘች ከተማ ናት። የተሰጣቸውን ጸጋ በአግባቡ በመጠቀም የኑሯቸው መሰረት ያደረጉት የከተማዋ ነዋሪዎችም ብዙ ናቸው።
“ቱሪዝም ተሰባሪ ነው” ይባላል። የመስሕብ ቦታው በጥንቃቄ ካልተያዘ መስህብነቱ ያበቃል፤ ጎብኝዎችንም በሰላም፣ በፍቅር እና በእንክብካቤ ማስተናገድ ካልተቻለ ወደዚያ ቦታ የሚዘልቅ ሰው ይጠፋል። የሚገኘው ጥቅምም ይቆማል ማለት ነው። ይሄኔ ነው ቱሪዝም ተሰበረ የሚባለው። የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች ቅርሳቸውን ይወድዳሉ፤ እንግዶቻቸውንም ተመልሰው እንዲመጡ በሚያስናፍቅ መልካም መስተንገዶ ይሸኛሉ።ይህ የቱሪዝምን ተሰባሪነት ጠንቅቀው የሚገነዘቡ ለመኾናቸው ምስክር ነው።

የላሊበላ ከተማ ነዋሪው ወጣት ማረልኝ አያልነህ “የላስታ ሕዝብ ከልብ የሚመነጭ ሰው ወዳድነትን የተላበሰ ነው፤ ይህም ራሱን ችሎ ሊጎበኝ የሚችል የቱሪዝም ሃብት ነው” ሲል ይናገራል። ወደ ላሊበላ የሄደን እንግዳ እግር አጥቦ መቀበል፣ መደብን ለቅቆ ማሳረፍ የሕዝቡ የቆየ ልምድ ነው ብሎናል ወጣቱ።

እንደ ወጣት ማረልኝ ገለጻ የላሊበላ ሕዝብ ለእንግዶች የሚያሳየው ክብር እና ፍቅር ከቱሪዝም ጥቅም ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይኾን ከልብ የመነጨ እና ከሰብአዊነት ባሕሪ ጋር የተቆራኘ ነው። እንዲህ አይነቱ ሰላማዊ እና የካበተ እንግዳ ወዳድነት እንኳንስ ከላሊበላ ውቅር አብያ ክርስቲያናት ድንቅ ጥበብ ጋር ተጨምሮ ራሱን ችሎም ቢጎበኝ የሚያንሰው ነገር የለም።

ወጣቱ ላሊበላ ለወትሮው የሚጎርፉላት ጎብኝዎች አሁን ርቀዋታል ሲል ተናግሯል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የሰሜኑ ጦርነት የፈጠረው ተከታታይ ወረራ እና አሁን ላይ ሄድ መለስ የሚለው የክልሉ የሰላም ሁኔታ ለላሊበላ ቱሪዝም መቀዛቀዝ ምክንያቶች ስለመኾናቸውም ጠቅሷል።
አሁን ላይ አካባቢው ሰላም ነው፤ የልደትን በዓል የሚያከብሩ እንግዶችም መግባት ጀምረዋል ብሏል። የአካባቢው ወጣቶች እና መላው ነዋሪዎች ርቀው የቆዩ እንግዶችን በተለየ ፍቅር እየተቀበሉ በማስተናገድ ላይ መኾናቸውንም ገልጿል። በከተማው ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ሳይቀር እንግዶችን እየተቀበሉ እግር በማጠብ የማሳረፍ ሥርዓቱን ተያይዘውታል ብሏል ወጣት ማረልኝ። “እንግዶቻችን በሰላም እየተቀበልን ነው፤ ማየት የሚፈልጉትን ነገር እያዞርን አስጎብኝተን፣ ማወቅ የሚፈልጉትንም አሳውቀን፣ በሰላም ለመሸኘት ሁሉም ወጣት በጋራ እየሠራ ነው” ሲል ገልጿል ወጣቱ።

“ሰላማችን ተመልሶ እንግዶቻችን ወደ ከተማችን መግባት መጀመራቸው አስደስቶናል” ያሉን ደግሞ በአነስተኛ ምግብ ቤት ሥራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ይመኝ ዘውዱ ናቸው። የቱሪስቶች መምጣት ባለሆቴሎች እና ሌሎችም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከሚያገኙት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በተጨማሪ ለከተማዋ አጠቃላይ መነቃቃት ጥቅም እንዳለው ገልጸዋል።

ወይዘሮ ይመኝ ልደትን በላሊበላ የሚያከብሩ እንግዶች መግባት መጀመራቸውንም ገልጸዋል። እንግዶችን ተቀብሎ የማስተናገዱ ሥራ በሁሉም የከተማው ነዋሪዎች መጀመሩንም አንስተዋል። አልጋ ተከራይቶ የማረፍ ኢኮኖሚያዊ አቅም የሌላቸውን እንግዶች በቤታቸው ተቀብለው ለማሳረፍ መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወንድምነው ወዳጀ የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በላሊበላ የማክበር ዝግጅት ተጠናቅቋል፤ እንግዶችም እየገቡ ነው ብለዋል። የከተማው እና የአካባቢው ነዋሪዎች በተለመደው ሥርዓት እንግዶችን እየተቀበሉ እያስተናገዱ እንደኾነም ጠቅሰዋል። “ወደ ላሊበላ መምጣት በረከት የሚያገኙበት፣ ጥንታዊ ጥበብን የሚያደንቁበት፣ በሰዎች እንግዳ ወዳድነትም የሚደነቁበት ነው” ብለዋል ከንቲባው።

ከሆቴሎች፣ ሎጂዎች እና ሬስቶራንት ባለቤቶች ጋር ውይይት ተደርጎ ጥራት ያለው እና እንደ እንግዶች ፍላጎት የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት መግባባት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል። በበርካታ ቁጥር በቡድን የሚመጡ ጎብኝዎች በሆቴሎች ለማደር ስለሚቸገሩ ሰፋ ያሉ ቦታዎች ተዘጋጅቶላቸው እየተጠበቁ ነው ብለዋል ከንቲባው። ከግለሰቦች ቤት እስከ መንግሥት ተቋማት ያሉ በሙሉ እንግዶችን እንደየፍላጎታቸው ለማሳረፍ ዝግጁ ስለመኾናቸውም አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአዋሬ አካባቢ የተገነባውን የአነስተኛ ወጪ ቤቶች ግንባታ መረቁ።
Next article“የሕዝቡን የመረዳዳት እና የመደጋገፍ እሴት ማስቀጠል ያስፈልጋል” ማማሩ አያሌው (ዶ.ር)