
ባሕር ዳር፡ የካቲት 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) ክሳቸው የተቋረጠላቸው ግለሰቦችም 63 ሆነዋል ብሏል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ፡፡
በየትኛውም ወንጀል የተሳተፉ አካላትን ክትትል በማድረግ በህግ ተጠያቂ ማድረጉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታውቋል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክሳቸው የተቋረጠላቸውን ግለሰቦች እና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ መግለጫ እየሰጠ ነው፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች በእሥር ላይ የሚገኙ 60 ግለሰቦች ክስ እንዲቋረጥ መንግሥት መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ትናንት ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህግ እንደገለጸው ደግሞ ሦስት ግለሰቦችን በመጨመር ክሳቸው የተቋረጠላቸው ግለሰቦች 63 መሆናቸውን ገልጧል፡፡ ከሜቴክ ጋር በተያዘ በሙስና፣ ከሰኔ 15 ክስተት እና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በያያዘ በቁጥጥር ሥር የቆዩት ግለሰቦች ናቸው ክሳቸው የተቋረጠላቸው ብሏል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ፡፡
ክሳቸው ከተቋረጠላቸው መካከልም የወንጀል ተሳትፏቸው ዝቅተኛ የሆኑ፣ የጤንነት ችግር ያለባቸውና ከህጻናት ጋር የታሰሩት ይገኙበታል፡፡
ውሳኔው የተላለፈው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል እንደሆነም ነው ተገለጸው፡፡
በሀገሪቱ የሰው ህይወት መጥፋት፣ ግጭት፣ መፈናቀል እና የሀይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት መከሰቱን ተከትሎ በእነዚህ ሁኔታዎች መረጃ የተገኘባቸው 1 ሺህ 682 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ሆነው ጉዳያቸው እየታየ መሆኑን መንግስት መግለጹ ይታወሳል፡፡
ነገር ግን ጉዳዩን ከብሔር ጋር በማያያዝና አሳልፎ ላለመስጠት በመሞከር እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን ጠቅላይ አቃቤ ህግ በመግለጫው አመላክቷል፡፡
በመሆኑም በየትኛውም ወንጀል የተሳተፉ አካላትን ክትትል በማድረግ በህግ ተጠያቂ ማድረጉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያመላከተው፡፡