
ባሕርዳር: ታኅሳሥ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪና የሰላም እና የፀጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው በወቅታዊ የክልሉ ጉዳይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም የክልሉ ሰላም በየጊዜው ለውጥ እያመጣ በእጅጉ እየተሻሻለ ነው ብለዋል። የመልካም አሥተዳደር ፣ የትራንስፖርት፣ የንግድ ሥራዎች እና አገልግሎቶች ተስተጓጉለው እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ላይ ከነበረው መስተጓጎል በመውጣት ወደ መደበኛ ሥራዎች መገባቱንም ገልጸዋል።
የክልሉ ሰላም እንዲመለስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያበረከተው ሚና ከፍተኛ መኾኑንም አስታውቀዋል። ባልተገባ ፕሮፖጋንዳ የተናጋው ሰላም እና የተሳሳተው አካሄድ ሁሉ እየተሻሻለ መምጣቱንም ገልጸዋል። የክልሉ የፀጥታ መዋቅርም መጠናከሩን ተናግረዋል።
የክልሉ ሰላም በእጅጉ መሻሻል ቢያሳይም አሁንም ሙሉ ለሙሉ የሕዝብን ሰላም ማረጋገጥ ተችሏል ማለት አይቻልም ብለዋል። አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ማኀበረሰቡ አሁንም እየተጎሳቆለ መኾኑንም አመላክተዋል። የተጀመረውን ሰላም ማፅናት እና ዘላቂ ማድረግ በቀጣይ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
ሕዝቡ የጋራ ምክክር በማድረግ ሰላም ይከበርልን፤ ደኅንነት ይጠበቅ የሚል ጥያቄ እንዳነሳም አመላክተዋል። መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራውን ይሥራልን የሚል ጥያቄ በስፋት እንደሚነሳም አመላክተዋል። ለሠራዊቱ እና ለመንግሥት የነበረው አስተሳሰብ እየተሻሻለና ከሕዝቡ ጋር በጋራ በመቆም ሰላምን የማረጋገጥ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከሕዝብ ጋር ውይይት በማድረግ ጥያቄዎች በሚፈቱበት ሁኔታ ዙሪያ መግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል። በጋራ አንድነት የተመሠረተች ኢትዮጵያን የመገንባት ሂደቱ እንዲጠናከር ከሕዝቡ ጋር እየሠራን ነው ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በነፍጥ እንደማይመለሱ መግባባት እየተደረሰ መኾኑንም አመላክተዋል። ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል። የመልካም አሥተዳደር እና የሥራ አጥነት ችግርን ለመፍታት እየተሠራ ነውም ብለዋል።
የተፈጠሩ ግጭቶች ውይይት ያስፈልጋቸዋል የሚል ጥያቄ ከሕዝብ ዘንድ መነሳቱን የተናገሩት አቶ ደሳለኝ የሕዝብን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የሰላም ጥሪ መታወጁንም አስታውሰዋል። የተደረገው የሰላም ጥሪ ሕዝብና መንግሥትን ያግባባ መኾኑንም ገልጸዋል።
የታጠቁ ኀይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ ሕዝቡ እየሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። በቀረበው የሰላም ጥሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ወደ ሰላም መምጣታቸውንም አንስተዋል። መንግሥት ለሰላም የገቡትን ሥልጠና እየሠጠ መኾኑንም ገልጸዋል። የሰላም ጥሪዉን የተቀበሉ ታጣቂዎች መፀፀታቸውን፣ ሕዝብን ይቅርታ መጠየቃቸውን እና ሕዝብን ለመካስ መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።
የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ወደ ሰላም የገቡትን የራሳቸውን የጦር መሳሪያ በመደበኛነት አስመዝግበው እንዲይዙ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። የተሃድሶ ሥልጠና የወሰዱ አካላት ለሰላም መስፈን አምባሳደር ኾነን እንሠራለን ማለታቸውንም ተናግረዋል።
በፀጥታው ችግር ምክንያት የተናጋውን መዋቅር የማስተካከል ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። የፀጥታ መዋቅሩን መልሶ የማደራጀት እና የማጥራት ሥራ መሠራቱንም ነው የተናገሩት። መልሶ ማደራጀቱንም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግም ነው ያብራሩት።
ለሕዝብ የቆመ፣ ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ የሚሠራ የፀጥታ መዋቅር መገንባት ያስፈልጋልም ብለዋል። ጠንካራ የፀጥታ ተቋም የመገንባት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።
እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ለሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል። የሰላም እና ደኅንነት ማጣት የሕዝብን ችግር እንደሚያበዛው ተናግረዋል። ሰላምን የሚያውክ ሁሉ በሕዝብ ላይ እየፈረደ መኾኑን ማሰብ ይገባዋል ነው ያሉት። የትኛውም ጫፍ የወጣ ጥያቄ ይኑር በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይገባል ብለዋል።
በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲከውኑ እየተሠራ መኾኑንም ነው ያስረዱት። ሁሉም ጥያቄዎች የሚፈቱት ያለውን በማፍረስ ሳይኾን ካለው ላይ በመጨመር ነው፣ በውይይት እና በመግባባት ጥያቄዎችን መፍታት ይገባል ነው ያሉት።
አቶ ደሳለኝ ሕዝቡ ለበዓል መዋያ የሚኾን ገንዘብ ለሠራዊቱ እያዋጣ መኾኑንም ገልጸዋል። ሕዝቡ እያደረገው ያለው ተግባር የሕዝቡን ጨዋነት የሚያስመሰክር እና ምሥጋና የሚገባው መኾኑንም ተናግረዋል።
አሁንም ጥቂት አካላት የሕዝብ ሰላም እንዲናጋ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የሕዝብን ሰላም ለማወክ የሚሠሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ነው ያሉት። በዓላትን ለማጠልሸት የሚሠሩ ሥራዎች ተገቢ አይደሉም፤ በዓሉን ለማወክ የሚሠራ ካለም አይሳካም ብለዋል። የፀጥታ ኀይሉ ሕግን ለማስከበር ዝግጁ መኾኑንም ተናግረዋል።
በኀይል የሚሳካ ነገር የለም፤ ይሄን አውቆ ሁሉም ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ በማብራሪያቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!