
ሁመራ: ታኅሳሥ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጤና መምሪያ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኀን የቅድመ ዝግጅት አፈጻጸም ግምገማ እና ውይይት በሁመራ ከተማ አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ጤና የሁሉም ነገር መሠረት ነው ብለዋል። የዞኑ ማኅበረሰብ በአነስተኛ ወጭ ጤናው እንዲጠበቅ ውጤታማ የጤና መድኅን አገልግሎት መዘርጋት አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል። ለዚህም ሁሉም ባለድርሻዎች በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሕመም ወቅት ድንገት ከሚፈጠር የጤና ወጭና ጭንቀት ኅብረተሰቡን ለማላቀቅ የጤና መድኅን አገልግሎት በዞኑ ለማስጀመር በቁርጠኝነት ሊሠራ ይገባል ብለዋል አቶ አሸተ።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ኅብረተሰቡ በአካባቢው የጤና መድኅን አገልግሎት ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አንስተዋል። ለማኅበረሰቡ ፍትሐዊ፣ ተዓማኒ እና ቀልጣፋ የጤና መድኀን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም ጠቁመዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ መንገሻ ንጉሱ በ2016 በጀት ዓመት ከ85 ሺህ በላይ የጤና መድኀን አባላት ለመመዝገብ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
በዞኑ የጤና መድኀን አገልግሎት አለመኖሩ በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ያስታወሱት የመምሪያው ኀላፊ አሁን ላይ የጤና መድኀን አገልግሎቱን ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል።
ፍትሐዊና ተዓማኝ አገልግሎት ለመስጠት የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረው የአገልግሎቱ መጀመር በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ደስታን ፈጥሯል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!