
ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት የሥራ ፕሮጀክት የሁለተኛ ምዕራፍ አንደኛ ዙር የዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ የገንዘብ ድጋፍ የማስተላለፍ እውቅና ሰጥቷል።
በ2014 ዓ.ም የተጀመረው የሴፍቲኔት ፕሮጀክት 1 ሺህ 61 የቤተሰብ መሪዎችን እና 3 ሺህ 305 የቤተሰብ አባላትን በድምሩ 4ሺህ 366 ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።
የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች የአካባቢ ልማት እና የጽዳትና ውበት ሥራ ይሠራሉ። በግላቸውም የከተማ ግብርና እና ሌሎች ሥራዎችን እየሠሩም ጥሪት እንዲያፈሩ እየተደረገ ነው። የንግድ ክህሎት ሥልጠናም ተሰጥቷቸዋል።
ተጠቃሚዎቹ ለሠሩበት ከሚከፈላቸው ክፍያ ላይም 26 ሚሊዮን ብር የቆጠቡ ሲኾን 12 ሚሊዮን ብር ደግሞ በፕሮጀክቱ ተቆጥቦላቸዋል። በፕሮጀክቱ ፕሮግራም መሰረት ተጠቃሚዎች ሥራ ፈጥረው ለማቋቋም የሚሰማሩበትን ሥራ መርጠው ሥልጠና ወስደዋል። ለሥራ ማስጀመሪያም ለእያንዳንዱ ቤተሰብ 26 ሺህ 750 ብር ይከፈላል። በቀጣይ ወደ ሥራ መግባታቸው ሲረጋገጥ 6 ሺህ 687 ብር ይለቀቃል።
የባሕር ዳር ከተማ ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ እመቤት መንግሥቱ የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ድህነትን በመቀነስ፣ በፍትሐዊ ተጠቃሚነት እና በከተማ ጽዳት እና ውበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል። የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች በድጋፉ እንዲለወጡበት ባለ ድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ዝቅ ብሎ ሠርቶ መለወጥ እንደሚቻል በተግባር የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል። “የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በሚያገኙት ገንዘብ ሠርተው እንዲለወጡ ከተማ አሥተዳደሩ አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል” ሲሉም ከንቲባው ገልጸዋል። ዘላቂ ልማት የሚኖረው በዘላቂ ሰላም ላይ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ የቀጣይ ጊዜያት ሃይማኖታዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ሁሉም ሕዝብ በጋራ ኾኖ ሰላሙን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።
ወይዘሮ ከተማ ደመወዝ የባሕር ዳር ነዋሪ እና የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ናቸው። ከፕሮግራሙ መጀመር በፊት በልብስ ማጠብ እና እንጀራ መጋገር ይተዳደሩ ነበር። በሴፍቲኔት ፕሮጀክቱ ክፍያ ከሚያገኙት የገንዘብ መጠን በላይ የተሰጣቸው ሥልጠናን ሥራ መፍጠር እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። ”ኮምፖስት ማዘጋጀት፣ በግ ማድለብ እና ሌሎችንም ገቢ ማስገኛ እየሠራን ነው” ያሉት ወይዘሮ ከተማ አሁን ላይ የሚፈልጉት የመሥሪያ ቦታ እንደኾነ ገልጸዋል።
ወይዘሮ ማማር ታከለ ከራሳቸው ጋር 4 ቤተሰብ ያስተዳድራሉ። ከመሰሎቻቸው ጋር ተደራጅተው ቆሻሻ የነበረን አካባቢ በማጽዳት ጨፌ አልምተው ይሸጣሉ። በየወሩ ዕቁብ በመጣል እና ባገኙት ሥልጠና በመሥራት ሕይወታቸው እየተሻሻለ መኾኑን ነው የተናገሩት።
”ለሰባት ዓመት የኖርኩበትን ቤት ምንም አልሠራሁበትም ነበር” ያሉት ወይዘሮ ማማር “አሁን ግን ባገኘሁት ሥልጠና በግ እያረባሁ እጠቀማለሁ” ብለዋል። በቀጣይም የዶሮ እርባታ እና የእንቁላል ምርት ላይ ለመሠማራት ሥራ መጀመራቸውንም አስረድተዋል።
የሁለተኛ ምዕራፍ አንደኛ ዙር የዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ የገንዘብ ድጋፍ 28 ሚሊዮን 381 ሺህ 962 ብር የሚለቀቅ ሲኾን ከአራት ወር በኋላ ደግሞ 7 ሚሊዮን 95 ሺህ 437 ብር እንደሚለቀቅ ታውቋል። በድምሩም 35 ሚሊዮን 477 ሺህ 399 ብር በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ለሚሰማሩ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች ይለቀቃል።
የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከአራት ዓመት በፊት ከዓለም ባንክ በተገኘ የ300 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እና ከኢትዮጵያ መንግሥት በተለገሰ 150 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ በ450 ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ በ11 ከተሞች መጀመሩ ተገልጿል። ፕሮጀክቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ እያደረገም ይገኛል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!